Tuesday, March 10, 2015

14ኛውን ዓመት የትህዴን ምስረታ በዓል የካቲት 19/2007 ዓ/ም በትህዴን ማሰልጠኛ ማዕከል በደመቀ ሁኔታ መከበሩን ሪፖርተሮቻችን ከቦታው ገለፁ።



    በቦታው የተገኙት ሪፖርተሮቻችን እንደገለፁት የየካቲት 19 የድርጅታችን የምስረታ በዓል “ዛሬም እንደትላንቱ ዋናው መፍትሄው የትጥቅ ትግል ነው” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ አካባቢዎችና ሰራዊታችን የሚገኙባቸው ቦታዎች በዓሉ በድምቀት መከበሩን የገለፀው መረጃው በተለይ በትህዴን ማሰልጠኛ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ መከበሩ ተገልጿል።
    በትህዴን ማሰልጠኛ ማዕከል የሚገኙ ሰልጣኞች። በላያቸው ላይ ተጭኖ የነበረውን የወያኔ ኢህአዴግ የጭቆና ቀንበር ለማስወገድ የህዝባችንን ችግር በመስዋእትነታችን መፍትሄ እናበጃለን በማለት አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያ ለመገንባት  ስልጠና ላይ የሚገኙት “አሰር” የተሰኙት ሰልጣኞች ታዳሚ እንግዶችና የትግሉ ደጋፊዎች በተገኙበት የካቲት 19/ 2007 ዓ/ም በድምቀት ማክበራቸውን መረጃው አመልክቷል።
    በበዓሉ ላይ የተገኘው የድርጅታችን ምክትል ሊቀመንበር ታጋይ መኮነን ተስፋይ በእለቱ እንደተናገረው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለጀግናው የትህዴን ሰራዊት እንኳን ለ14ኛው ዓመት የትህዴን ምስረታ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን ካለ በኋላ ዛሬ ባገራችን ውስጥ ያለው እውነታ ወያኔ እንደሚለው  ህዝቡ በልማትና በእድገት ላይ ሳይሆን መገዳደል፤ መወነጃጀል፤ ስደት፤ በወገናዊነት የሚፈፀም አድልዎ የተስፋፋበትና የወያኔ ባለስልጣኖች ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የአገርና የህዝብን ሃብት እንዳሻቸው የሚመዘብሩበት በአንፃሩ ጭቁኑ ህዝብ ደግሞ አስከፊ ኑሮ የሚገፉበት ሁኔታ ነው ያለው ሲል ገልጿል።
    በማሰልጠኛው ውስጥ የሚገኙ ሰልጣኞች በበኩላቸው የካቲት 19 የድርጅታችን የምስረታ በዓል በደማቅ ሁኔታ እያከበሩት መሆናቸውንና በዚሁ እለት ለበለጠ ትግል ቃል የምንገባበት እለት ነው ሲሉ መናገራቸውንም ከሪፖተሮቻችን ጋር ባደረጉት አጭር ንግግር ለመረዳት ተችሏል።
    በመድረኩ የተገኙት ዓወት ንውፅዓትና ማእበል የተሰኙት የትህዴ የባህል ቡድን ህዝቡ በስርዓቱ ላይ የሚያደርሰውን ጭቆናና የታጋዮቻችንን አኩሪ ገድል የሚያንፀባርቁ አዳዲስ ዘፈኖችንና ድራማዎችን መድረኩ ላይ በማቅረብ ለበዓሉ የተለየ ድምቀት መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
   የተከበራችሁ አድማጮቻችን/ ተመልካቾቻችን/ በተለያዩ አካባቢዎች በሰራዊታችን ውስጥ የተካሄዱ የበአሉን አከባበር አስመልክተን ልዩ ዝግጅት እንደደረሰን እናቀርብላችኋለን።