Wednesday, May 20, 2015

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን የሚገኙ የህወሃት ኢ.ህ.አ.ዴግ ካድሬዎች ነዋሪው አርሶ አደር ያፈራውን ምርት ያለፈቃድ ያመረታችሁት ነው በማለት ቀምተው በጨረታ በመሸጥ ለራሳቸው እንደተከፋፈሉት ለማወቅ ተችሏል።



    በተጠቀሰው ዞን ልዩ ቦታ እድሪስ በተባለው ቦታ የሚገኙ የህወሃት ኢ,ህ,አ,ዴግ ተላላኪ ካድሬዎች በዜጎች ላይ ግፍ እየፈፀሙ መሆናቸውን የገለፀው መረጃው በመሆኑም ያለፈቃድ መሬት አረሳችሁ የሚል የሃሰት ምክንያት በመፍጠር ባለፈው መጋቢት ወር 2007 ዓ/ም ተላላኪ ካድሬዎች ከድሃው ወገናችን 1660 ኩንታል ሰሊጥ ቀምተው በጨረታ የሸጡት ሲሆን ይህንን ተግባር ለፈፀሙ ስካውት 15,000 ብር በፀረ ሽፍታ ለሚታወቁ የስርዓቱ ደጋፊዎች ደግሞ 10,000 ብር ከተሸጠው በሽልማት መልክ ከካድሬዎች የተበረከተላቸው መሆኑ ታውቋል።
    ከዚህ አካባቢ ሳንወጣ በአዲጎሹ በ2006 ዓ/ም  “የሰፋሪዎች ማህበር” ተብሎ የሚጠራ በገዥው መንግስት የተደራጀ ማህበር መቋቋሙን የገለፀው መረጃው ዜጎች እየደረሰባቸው ያለውን በደል ለመክሰስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄዱ ባለጉዳዮች ጉዳያቸው ተጣርቶ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከሚታይ ይልቅ ወደ ተቋቋሙት ማህበሮች እየተመራ የማህበሩ ሊቀመናብርት እያዩት መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
   ይህ ማህበር ወርቅ ለቃሚወችንና ተንቀሳቃሽ አርሶ አደሮችን ለመቆጣጠር ታልሞ የተቋቋመ ህገወጥ ማህበር ሲሆን ጉዳያቸውን ለመስማት ከ300 ብር በላይ እየከፈሉ ፖሊስ፤ ምልሻ ፀረ ሽፍታና ስካውት ተብለው በስርዓቱ የሚጠሩ ተካፍለው እንደበሉት ታውቋል።
      ፀረ ህዝብ ተግባር ከሚፈፅሙት ተላላኪዎች  መካከልም የአዲጎሹ ቀበሌ አስተዳዳሪ የኛው ደርበው፤ የፖሊስ ሃላፊ አብርሃ፤ የፀጥታ አባል ገብረሂወት ወዲ እገላ፤ በአድጎሹ የሰፋሪዎች ማህበር ሃላፊ እድሪስ ኢብራሂምና የስካውት ሃላፊ ፋቲንጋ ፀጋይ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ጨምሮ አስረድቷል።