Friday, May 29, 2015

የህዝቡን ደህንነት የሚጠብቅ የወያኔ ኢህአዴግ የውጭ ፖሊሲ!!



አንድ መንግስት ጠንካራና አስተማማኝ የውጭ ጉዳይ ፖሊስና ብሄራዊ ደህንነት ቀይሶ የህዝብንና የሀገር ሉአላዊነት፤ ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ እንዲሁም የሃገሪቱን ጥቅምና ፍላጎቶች ለማስከበር የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል።
   ከዚህ አንጻር የኢህአዴግ ስርዓት በአገራችን ውስጥ እየሰራበት የሚገኘው የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች ምን ይመስላልና መሰራት ወይም መፈፀም አለባቸው ተብለው ከሚገለፁ ዋና ዋናዎቹ እንኳን ለማየት ብንሞክር አብዛኛዎቹ ባፈፃፀም ላይ ለፕሮፖጋንዳ ተብለው ከሚገለፁት ውጭ የህዝቡንና የሃገሪቱን ክብርና ጥቅም በሚያስጠብቁ መንገድ ሲሰራባቸው አይታይም።
   የኢህአዴግ ስርዓት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው በማስፈፀም ላይ ትኩረት እያደረግሁ ነው ብሎ ካስቀመጣቸው መካከል።
-    የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ማእከል ማድረግ፤
-    የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት አስተዋፅኦ መፍጠር፤
-    ፈጣን የኢኮኖሚ ልማትና ብልፅግና ለማምጣት ጥረት ማድረግ፤
-     ሰላምና መረጋጋትን መፍጠርና አጠቃላይ ፖሊሲዎችን ማስፈጸም፤
-        ብቃት ያላቸው አስፈፃሚ አካላት በቦታው በማሰማራት ፖሊሲዎቹን መተግበር የሚሉና ሌሎችም ቢሆኑም ስርዓቱ ግን በሚያስገርም ሁኔታ በ24 ዓመት የስልጣን አገዛዙ ውስጥ አንዱን እንኳን ለማስፈፀም አቅምና ችሎታ ማጣቱ  ነው።
    የአገራችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪይ ቤት የአንድ ፓርቲ ጥቅም ማእከል ያደረገና የኢህአዴግ ጉዳይ አስፈፃሚ በመሆኑ የስርዓቱ ታማኞች በከፍተኛ ሁኔታ የተሰገሰጉበት ቦታ ስለሆነ በተለይ በውጭ የሚገኙ ኢምባሲዎችና የዲፖሎማት ሰራተኞች የስርዓቱ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ለመሸፈንና ዲያስፖራው ላይ የተዘረጋውን የስለላ መዋቅር ለመከታተልና ለማስፈፀም እንጂ የአገሪቱን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩና ከአገሮች ጋር ሊኖር የሚገባውን ጤነኛ ግንኝነት እየፈጠሩ እንዳልሆነ ይታወቃል።
   ስርአቱ የህዝቡን ደህንነትና ጥቅም በማያስጠብቅ መልኩ እየሰራበት ካለው አንዱ በኢንቨስትመንት አጠቃቀም ዙሪያ ነው ባሁኑ ግዜ ብዛት ያላቸው የውጭ ባለ ሃብቶች ወደ አገራችን እንዲገቡ እየተደረገ ነው፣ ነገር ግን ይህ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የአገር ልማትና እድገት ታይቶ እየተፈጸመ ያለ ሳይሆን በፖለቲካ ጠቃሚነቱ ብቻ እየተሄደበት እንደሆነ ይታወቃል።
    ዛሬ አገራችን ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት መሆን የነበረበት ሊለማ በሚፈለገው አካባቢ እንጂ ዜጎቻችን ለመኖርያ ቤት መስሪያ እንኳን አጥተው ችግር ላይ በወደቁበት ግዜ በከተማ ውስጥ ለኢንቨስተሮች ተብሎ ከ 60 እስከ 70 የሚገመት ሄክታር እንዲሰጣቸው እየተደረገ ነው።
    አገራችን ኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ባለው የክህደት አስተሳሰብ የተጠናወተው ፀረ ህዝብ ስርዓት ምክንያት ዜጎቻችን አገራቸውን ጥለው እየኮበለሉና በየሄዱበት አካባቢ አስቸጋሪ ህይወት እያሳለፉ እንደሚገኙና ከውጭ አደጋ ተገላጭነት የዳኑበት ሁኔታ ያለመኖሩን የሚያሳይ ብዙ ማሳያወች ሊቀርቡ ይችላሉ።
    ከሳውዲ አረብያ ሰብአዊነት በሌለው ሁኔታ ሰርተው ያፈሩትን ሃብትና ንብረት እንኳን ሳይዙ ከመንገድ ተለቅመው ወደ አገራቸው የተመለሱ ዜጎች፤ ሊቢያና ደቡብ ኣፍሪካ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ህይወታቸውን ያጡ ንፁሃን ወገኖች፤ ባለፉት አመታት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ በኮንቴነር ታፍነው የሞቱና አሁንም የመን ውስጥ በተከሰተው ጦርነት ሳብያ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችን መንግስት ቀልጣፋ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት መጥፎ ሁኔታ ላይ የወደቁና ባህር አቋርጠው ለመሰደድ በሚሞክሩ ሌሎች ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው አሳዛኝ እልቂት የኢህአዴግ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ እንዝላልነትን የሚያሳይ መሆኑ እንጂ ሌላ ትርጉም ሊያሰጠው አይችልም።
    ባጠቃላይ- ህዝቡ ባገሩ ላይ ሰርቶ እንዳይበለፅግ፤ አገሪቱ ውስጥ ባለው ብልሹ ፖለትካዊ ሁኔታ ተገዶ እንዲኮበልል፤ ወጣቱ ተምሮ የስራ እድል እግኝቶ እንዳይሰራ፤ ሁሉም ነገር ድርጅታዊ በሆነ አሰራር ስለሚፈፀምና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በእጅጉ ስለተስፋፋ  በተለይ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቶ ባለበት ግዜ የኢህአዴግ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲው በመልካም ሁኔታ ነው ያለው ብሎ መነገሩ ለህዝቡ ያለውን ንቀት ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ነው።