Sunday, October 4, 2015

በደቡብ ክልል በሀዲያ ዞን “አባ ሰንጋ” የተሰኘው የከብቶች በሽታ ተከስቶ በርካታ ሰዎችና ከብቶች ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።



የተለያዩ ምንጮች እንዳስታወቁት እስካሁን በበሽታው አስራ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ገልፆ። በበሽታው እጅግ በርካታ ከብቶች እያለቁ በመሆናቸውም የአካባቢው ህዝብ የመስቀልን በዓል ጨምሮ በተለያዩ ክብረ በዓላት ከስጋ ተዋጽኦ ውጪ እንዲከበር መወሰኑን አስረድቷል።
በአሁኑ ወቅት ለተወሰኑ ከብቶች ክትባት መስጠት የተጀመረ ቢሆንም  በሽታው በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። ከመስቀል በዓል ጋር ተያይዞ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት መፈጠሩንም ምንጮቹ አክለው ገልፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በሽታው ወደ ሌሎች ኣካባቢዎች እንዳይዛመት ያደረጉት ጥረት ባለመኖሩ ነዋሪዎቹ በስርአቱ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳሳደሩ ተገልጿል።