የህዝቡ መብት የሚረጋገጠው የነጠረ ህዝባዊ መስመርና ሃገራዊ ፍቅር ያለው
ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው።
ህዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆ ባገራችው ውስጥ በሰላምና በመተሳሰብ
መኖር ከተሳናቸው፤ ያገራቸው ሃብት ተጠቃሚ ሆነው ያለ አድልዎ በእኩል
ለመኖር ካልቻሉ፤ የመሰላቸውን ሃሳብ ሊገልፁና ያሻናል የሚልቱን ደግፈው የሚቃወሙትን ደግሞ ነቅፈው የሚሄዱበት ፍትሃዊ አሰራር ካልተመቻቸላቸው
የብሄር ብሄረስብ መብት አስመልክቶ ብዙም ቢነገርና ቢለፈፍ ፋይዳ የለውም።
በአገራችን ውስጥ ያለው ፀረ ህዝብ ስርዓት። በቀጣይ የስልጣኑን እድሜ
ለማራዘም ሲል መጨረሻ የሌላቸው ክብረ በአላት በመደርደር ህዝቡን ሳያምንበት በማስገደድ የሸፍጥ ነጋሪት ስያስጎስም ማየት የተልመደ
ተግባር ሆኖ እየቀጠለ ነው፣ ቢሆንም በነዚህ የማደናገርያ በዓላት እርካታ ያገኘና ለጥያቄው መልስ ያገኘ ህዝብ ግን ከቶም አልተገኘም።
የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት በየአመቱ በአላት በመደርደር ህዝቡን ሲያደናግርና
የሚፈፅመውን ፀረ ህዝብ ተግባር በመሸፈን ለህዝቡና ለሃገሩ እንደሚያስብ አስመስሎ የሚያቀርበው ምክንያት ሆን ብሎ ስልጣኑን ለማስቀጠል
በማሰብ ነው። ነገር ግን በሁሉም ያገሪቱ አካባቢዎች በሚፈፅማቸው ፀረ ህዝብ ተግባሮች ፈፅሞ ለመደበቅ እንዳልቻለና በተለያዩ ያገሪቱ አካባቢዎች ስርአቱን በመቃወም ዓመፅና ግጭቶች እንዲከሰቱ ምክንያት እየሆኑ
እንደሆኑ ግን የሚካድ አይደለም።
በአሁኑ ሰዓት የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት-
- በጉያው ውስጥ ሆነው የሚታገሉትን የተቃዋሚ
ድርጅት አባላትና አመራሮች የተለያዩ የሃሰት ወንጀሎችን በመለጠፍ እየፈፀመው የሚገኘው ትግሉን የማኮላሸት ተግባር በሚካሄደው አስመሳይ
ምርጫ ላይ ብቻውን ተወዳድሮ አሸነፍኩ ለማለት እያደረገው ያለ መሰሪ እንቅስቃሴ፤
- የሃይማኖት መሪዎችንና የቤተ ክርስትያን
አገልጋዮች የሆኑ ቄሶች ሳይቀር የተቃዋሚዎች ደጋፊዎችና ተባባሪዎች ናችሁ በማለት እያካሄደው የሚገኘው የማስፈራራትና የማሰር እርምጃ፤
- በያዝነው አመት ውስጥ በተለይ 2007 ዓ/ም
በሚደረገው ምርጫ ላይ ግምት በማስገባት በስርአቱ የበላይ ባለስልጣኖች በየደረጃው ለተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍል በመሰብሰብ በሚያደርጉት
ቅስቀሳና ተሳታፊው ህብረተሰብ ጫና በተሞላበት የውዴታ ግዴታ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ለሚያቀርበው ጥያቄ እንደ ፀረ ህዝብና የልማት
አደናቃፊ አድርገው በመቑጠር በላዩ ላይ ችግሮች መፈፀም።
- ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ላስቀመጧቸው
ተቃዋሚዎች። በተለይ በህዝቡ ላይ ተቀባይነት ካገኙ በህብረተሰቡ መሃል ግጭት እንዲፈጠርና የሰው ህይወት እንዲጠፋ ካደረጉ በኋላ
ሆን ብለው ህዝቡን በማደናገር ግጭቱ ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዳቀነባበሩት በማስመሰል ከህዝቡ እንዲነጠሉ ለማድረግ መሞከር፤
- ሕብረተሰቡ! ስርአቱ በንፁሃን ህዝብ ላይ
የሚያካሂዳቸውን መሰሪ ተግባሮች ጠንቅቆ የሚያውቀው ቢሆንም የወያኔ ካድሬዎች ግን እንደተለመደው ሲያካሂዱት የቆዩትን ፕሮፖጋንዳ
አጠናክረው በመቀጠል በተለይ በያዝነው ወር የራሳቸውን ፀረ ህዝብ አሰራር በመሸፋፈን ያለፉትን ስርዓት በሚወቅስ መንገድ የሚያካሂዱትን
የሸፍጥ ቅስቀሳ ወዘተ… የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦችን መብት መከበርን የሚያሳይ ሳይሆን ይበልጥ በህዝቡ ላይ እየፈጸሙት የሚገኙትን
አፈና፤ የመብት ጥሰትና ሌሎች ፀረ ዴሞክራሲያው ተግባሮች አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
ስለዚህ! ይህ ስርዓት የብሄር ብሄረሰቦች መብት የሚያከብር፤ የህዝቡን
ጥያቄ የሚያዳምጥ፤ ለማስመሰል ተብሎ ሳይሆን ከእውነት ተነስቶ ተግባር ላይ ለማዋል የሚንቀሳቀስ፤ የህዝቡን ስሜት በማዳመጥ ከህዝቡ
ጋር ተማክሮና ተነጋግሮ የሚሰራ፤ የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብ በማስወገድ የህዝቡን ጥቅም ለማስከበርና ያለምንም ልዩነት መልካም
አስተዳደርን ለማስፈን ጥረት የሚያደርግ ስርአት ስላልሆነ የብሄር ብሄረሰቦች መብትና እኩልነት ያስከብራል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም።