ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ/ም የተካሄደው
ሃገራዊና ክልላዊ የይስሙላ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ማጭበርበርና ማስፈራራት እንደነበረው የገለፀው መረጃው በተለይም በሓድነት ከባቢያዊ
አስተዳደር በአይደርና በ09 ቀበሌ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ህዝቡ መርጦ ከሄደ በኋላ ድምፅ በሚቆጠርበት ጊዜ የገዥው ስርዓት ካድሬዎች
ቆጠራውን አቋርጠው ታዛቢዎችንና ቆጣሪዎችን የእራት ሰዓት ደርሷል በማለት አጭበርብረው የስርቆት ስራ መስራታቸውን ከስፍራው የደረሰን
መርጃ አስረድቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን የማጭበርበርና የመስረቅ ስራ ለመስራት ታዛቢዎችንና
ቆጣሪዎችን መጠን የሌለው ቢራ እንዲጠጡና እንዲሰክሩ በማድረግ የድምፅ ኮሮጆውን ወረቀቱን በመገልበጥና በመውሰድ ራሳቸው ያስቀመጧቸው
የህወሃት ኢህአዴግ ካድሬዎች ሙሉ በሙሉ ድምፅ ያገኙ በማስመሰል ሰነድ አዘጋጅተው በማስገደድ እንዳስፈረሟቸው ለማወቅ ተችሏል።
በመጨረሻም በታዛቢነት የተቀመጡ ወገኖች ሁኔታው በመጨረሻ ስለተረዳቸው
ለምን እንደዚህ አይነት ተግባር ይፈፀማል ባሉበት ጊዜ ይህ የምትሉን ነገር በውጭ ወጥታችሁ ከደገማችሁት እወቁ ወድዳችሁ በፈረማችሁበት
ተጠያቂ መሆናችሁ ይረዳችሁ ለህይወታችሁ ህልውናና ለቤተሰቦቻችሁ አስቀድማችሁ አስቡበት እያሉ እንደ አስፈራርዋቸው ታውቋል።