በአማራ ክልል፤ አዊ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ከህዳር 12
/2007 ዓ/ም ጀምሮ የአርሶ አደሮች ኮንፈረንስ በተካሄደበት ጊዜ በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ ላይ ልናሸንፍ ከተፈለገ
ያሉንን ችግሮች መገምገም ይኖርብናል የሚል አጀንዳ ይዘው ኮንፈረንስ ባካሄዱበት ሰዓት በርካታ የተቃውሞ ጥያቄዎች እንደተነሱ ለማወቅ
ተችሏል።
በወቅቱ ከተነሱት ጥያቄዎችም የማዳበርያ ዋጋ መጨመር፤ የገጠር መንገድ
እጥረት፤ የመብራትና የትምህርት ጥራት ችግሮችን አስመልክተን ለ23 ዓመታት ያህል በተደጋጋሚ ግምገማ ብናደርግም የታየ ለውጥ ግን
የለም! እነዚህ ጥያቄዎቻችን ካልተመለሱ ደግሞ በግንቦት ወር ላይ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ ሊሆን አይችልም በማለት ተቃውማቸውን
የገለፁ ሲሆን ለጥያቄአቸውም ተገቢ መልስ አለማግኘታቸውን ያገኘነው መረጃ አስታውቋል።
ይህ በንዲህ እንዳለ ከህዳር 17/2007 ዓ/ም ጀምሮ የመምህራን ኮንፈረንስ
በሚል ለተከታታይ 5 ቀኖች ዳይሬክተሮችና ሱፐር ቫይዘሮች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ደመወዝ አንሶናል፤ ትምህርት ቤቶቹ የወንበር እጥረት
አለባቸው፤ የትምህርት መገልገያ መሳሪያዎች እጥረት አለ በማለት። አቤቱታቸውን በምሬት እንደገለፁ ለማወቅ ተችሏል።
ተሰብሳቢዎቹ አክለው። በተለይ ጉርጃ፤ ጃንጉታና ባንጃ በተባሉ አካባቢዎች
ያለው የአስተዳደር ችግር ካልተፈታ ህዝቡ ኢህአዴግን መመረጥ እንደማይችል መግለፃቸውንና መድረኩን በመምራት ላይ የነበሩት የወረዳዋ
የመሬት አስተዳደር አቶ የትዋለ አንዱአለምና የግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ብርሃኑ
አያሌው ለቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢ መልስ እንዳልሰጡባቸው መረጃው
አክሎ አስረድቷል።