እንደሚታወቅ አገራችን ኢትዮጵያ ከሳህራ በታች
ካሉ አገሮች በድህነትዋ ግምባር ቀደም እንደሆነችና መሪዎችዋ ከዚህ የድህነት አረንቛ ለማውጣት ከፕሮፖጋንዳ ያለፈ ግብራዊ ተነሳሽነት
እንደሌለ ማንኛው ዜጋ የሚያውቀው ሃቅ ነው።
በዚህም የተነሳ ህዝቦችዋ በተለያዩ በሽታዎች
ሲለከፉና ተለክፎውም እንደሚሞቱ የታወቀ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ነፍሰ ጡር በቃሬዛ ተሸክሞ አዋላጅ ፍለጋ ቡዙ ማይሎች
ማቋረጥና መንከራተት ዛሬም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያልተነካና ያልተቀረፈ ችግር ነው። የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን በሰፊው እያሰማራሁ
ነው የሚለው የስሙላ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገና ያልደረሰባቸውና መፍትሄ ያላገኘላቸው የኤችአይቪና የካንሰር ይቅርና በወባ በሽተኞች
ተይዞ የሚሳቃይና የሚሞት ዜጋ ቁጥርም ቀላል አይደለም።
ባለፉት አመታት ከድርቅ ጋር በተያያዘ ለርሃብ
ከተጋለጡት ከ13 ሚልዮን በላይ ዜጎች ውስጥ ለበሽታ ችግር የተጋለጡትም ገዢዉ ስርኣት የቁጥር መከራከርያና መጫወቻ ካርድ አድርጓቸው
ነበር። ከጤና ጋር በተያያዘ በየጊዜው ለሚታይ ችግር አንዱ የመፍትሄ አቅጣጫ በቂ የሆነ የጤና ባለሞያ በየክልሉና በየገጠር ወረዳዎች
እንዲዳረስ ማድረግ ነው፣ ሰሞኑን የተሰማው ዜና ግን እጅግ የሚገርም ነው። እሱ ደግሞ መንግስት ነርሶችን እያሰለጠነ ለውጭ ገበያ
የማቅረብ እቅድ ይዞ ሊሰማራ ነው መባሉ “ሳይተርፋት ስታበድር ሳትቀበል
ሞተች” ለሚባለው ተረት እውነት የሚያደርግ ነዉ።
ዛሬ የአለም አቀፍ ሽያጭ ጉዳይ የተነሳባቸው
የነርሶችም ስደት ቁጥር ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር የኣገራችን ከፍተኛው ምጣኔ ይይዛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰለጠኑት ነርሶች መካከል
16.8 በመቶ የሚሆኑት በስደት ላይ የሚገኙ ናቸው። ያፈጠጠውና የገጠጠው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ አገሪቷ በባለሞያዎች፥ በቁጥርም
በጥራትም ራሷን ሳትችል የባለሞያ ሽያጭ ውስጥ እንድትገባ መታሰቡ መንግስት አሁንም በጥናት ላይ የተመሰረተና ዘላቂ የሆነ መፍትሄ
ማምጣት በሚችል እቅድ ላይ ከመሞርከስ ይልቅ ከድንገቴ እቅድ አተገባበር ሊወጣ አለ መቻሉን በግልፅ የሚያሳይ ነው።
ይሁንና ይህ እቅድ ተግባራዊ ሆኖ የሚቀጥል
ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኃላ ክትባት የሚሰጥ ባለሞያም ሃኪም ማግኘት ህልም ይሆናል። ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጤና ችግር
ለመፍታትና የጤና ባለሞያዎች ፍልሰት ለመቀነስ ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልጋል የሚል በቡዙ አቅጣቻ ተማፅኖ ሲቀረብ ነበር። ይሁንና ችግሩን
ለመቅረፍ ከቀረበው የፖሊሲ አማራጭ ይልቅ መንግስት ነርሶችን በመላክ የንግዱ አንደኛው ተዋናይ በመሆኑ ከሃሳቡ በተቃራኒ ቆሟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖሊሲዎችና የአሰራር እርስ
በርስ መጋጨት እየበዛ ነው። ስለ አምስት አመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ መስበክ የጀመረው ኢህአዴግ አገሪቷን ጥበብ ከተሞላበትና
መሬት ላይ ያለውን እውነታ ካገናዘበ መፍትሄና እቅድ ይልቅ በታአምር ወደፌት ሊያሸግራት ኣንደሚችል የሚያሳየው በተቃራኒው ውስጥ
ሆኖ ነው፣ ከዚህም ባለፈ የስራ አጥ ቁጥሩ ምጣኔ በአመት በ20 በመቶ እየተመነደገ ኢህአዴግ የጉልበት ሰራተኞችን ጭምር ከውጭ ለማስመጣት
ያቅዳል፥ ከመቶ አመታት በፊት የተዘረጋ የባቡር መስመር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ያለ አሳቢና ያለ አስተዋይ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች
እንኳ ሳይጠገን ተዘግቶ፥ በድንገት ከ6 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን የባቡር መስመር ለመዘርጋት አምስት አመት ብቻ በቂ ነው የሚል
ሃሳብ ይደመጣል። በሚቀጥለው 15 አመታት ውስጥ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት እናደርሳታለን የሚለው የኢህአዴግ ዲስኩር
ተነግሮ ሳያበቃ በሸቀጦች የዋጋ መናርና በፖለቲካ ነፃነት እጦት ኑሮውን መቋቋም የከበደው ማህበረሰብ በሚኖርባት አገር ኣንደዚህ
አይነት የከሰረ የፖለቲካ ጨዋታ መጫወቱ ምንኛ በህዝብና በአገር ላይ ቁማር እየተጫወቱ መሆናቸውና ለይመሰል ተብሎ የተፈበረከ አስተዳደራዊ
ዝግጅት መሆኑን ሁሉም ኢትዮጳያዊ ዜጋ ሊያውቀው ይገባል።
በመጨረሻም ያለነ የሌለ ሃሳብ እያመጡ ህዝቡን
ሊያጠምቁት ቁጭ ብድግ በማለት ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ ካድሬዎች ተመልሶ
እነሱን ይዞ ወደ ገደል አፋፍ ላይ እንደሚጥላቸው ከታሪክ ሊማሩ ይገባል።