Sunday, March 8, 2015

የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት: በአርበኞች ስም የሚነግድ ቡድን ነው፣



   የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል በተለይ የትግራይ ወጣቶች ገድል በአለም ውስጥ ከተካሄዱ አስደናቂ ህዝባዊ ትግሎች አንዱ መሆኑንና ታሪኩ በተደጋጋሚ ቢነሳም ለኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት ነው። ያለፈውን ወርቃማ ታሪክ ክብር በመርገጥና ለጥቂት አለቅላቂዎች በሚገልፅ መንገድ ብቻ አቆነጃጅቶ ማቅረብ ግን በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አያድንም።
     በወያኔ ኢህአዴግ አምባገነን ቀጥተኛ አመራር ተደራራቢ ችግር ተሸክሞ እንዲጓዝ የተገደደው ህዝባችን ከፍተኛ በሆነ የአፈናና ረገጣ ራሱን አጎንብሶ የመከራ ፅዋ ቀማሽ እንዲሆን ህሊናው መቀበል እምቢ ስላለው በላዩ ላይ ይደርስበት የነበረውን ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና ከስር መሰረቱ ለመገርሰስ ሲል በጀመረው ትግል የደርግን ስርዓትን በሚያስገርም ብቃት ደምስሶታል።
    ነገር ግን 65 ሺህ ህይወት የከፈሉ ጀግኖች ሰማእታትና ከአንድ መቶ ሺህ በላይ አካላቸው የጎደሉበት ትግል ለ17 ዓመታት የተካሄደውን መራራ ትግል የደርግ ስርዓት ከተደመሰሰ በኋላ ያ ሁሉ ህዝብ የታገለለትን አላማ ክደው ለግል ጥቅማቸው በሚሯሯጡ ጥቂት ስስታም መሪዎች  የህዝቡ ድል ተነጥቋል።
     የደርግ ስርዓት በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተባበረ ክንድ ላንዴና ለመጨረሻ ከተገረሰሰ በኃላ ግን በወቅቱ የነበረው መድረክ አንዱን ጅብ አባርረህ ሌላኛውን ተኩላ እንደመተካት  ሆኖ ስለ ቀረ  ህዝቡ  የተሻለ ስርዓትና አስተዳደር ማግኘት አልቻለም። ያን ሁሉ መስዋእት የከፈለው ታጋይ ህዝባችን የትግሉ ፍሬ የሆነውን ሰላም፤ ፍትህና ዴሞክራሲ ማግኘት ሲገባው በዝባዥ በሆነው የኢህአዴግ ስርዓት መራራውን የኑሮ ሁኔታ እንዲያሳልፍ ተፈርዶበታል።
   ያገራችን ብሄር ብሄረሰቦች በቋንቋው እንዳይጠቀም፤ የትምህርት እድል እንዳይሰጠው፤ ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቱን ሳይጠበቅለት ለዘለዓለም በድንቁርና ዓለም ላይ እንዲዘፈቅ ባጠቃላይ በላዩ ላይ የታወጀውን የጥፋት ብይን ታግሎ መጨረሻው ላይ ቢያደርሰውም የኢህአዴግ ሽማምንቶች ግን በትግሉ ወቅት ለህዝቡ ቃል የገቡለትና የማሉለትን ልሳናቸውን ረስተው ሳይውሉ ሳያድሩ የደርግ አምሳያ ሆነው ፋሽስታዊ ዱላቸውን ለማንሳት ግዜ አልወሰደባቸውም።
    በዚህ ምክንያትም ባገራችን የዴሞክራሲ ስም እንጂ የዴሞክራሲ ፍሬ እንዳይታይ፤ ባገራችን ውስጥ ግርግር እንዲሰፍንና ዜጎቻችን የተረጋጋ ህይወት እንዳይኖራቸው ዋነኛ ተዋናዮች ሆነው እየቀጠሉ ናቸው።
    ህዝቡ እንዳለፈው በስርዓቱ አስገዳጅነት ከመኖርያ ቤቱ እየተፈናቀለና  የእርሻ መሬቱን እየተነጠቀ  ድብቅና ግልፅ በሆኑ እስር ቤቶች ህጋዊ ባልሆነ የፍርድ ሂደት እንዲሰቃይ ሲደረግ በአንፃሩ የስርአቱ ካድሬዎች ደግሞ ዜጎች በራሳቸው ፍላጎትና ተሳትፎ የተቀረጸውን ህገ-መንግስት እየተዳኙ ናቸው ብለው መናገራቸው በህዝቡ ላይ ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው።
     የተከበርህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ በስምህ እየነገዱ በላይህ ላይ ፖለቲካዊ ቁማር እየተጫወቱ የሚገኙትን አምባገነን የኢህአዴግ መሪዎች የጀግንነትህን ውሎ እያነሱ የአዞ እንባ እያነቡና በሰራኸው ህያው ታሪክ እየቀለዱ የስልጣን እድሜያቸውን ለማስረዘም አስበው እያካሄዱት ያለውን እንቅስቃሴ ቀና ከሆነ አስተሳሰብ ተነስተው የሰራኸውን ጀግንነት አስታውሰው ክብር ለመስጠት አስበው ሳይሆን በስምህ እየነገዱና በማይጨበጡ ተስፋዎች እጃቸው ውስጥ እንድትገባ በማድረግ የስልጣን እድሜያቸውን ለማቆየት ካላቸው ፍላጎት መሆኑን ተረድተን የተንኮል ሚስጥራቸው ልናጋልጣቸውና ይበቃችኃል ልንላቸው ይገባል።