Wednesday, October 8, 2014

ቀደም ሲል በጎንደር ከተማ በሞቱት የፖሊስ አባላት እጅ አለባቸው ተብለው በእስር ቤት ሲሰቃዩ የነበሩ ዜጎቻችን እየደረሰባቸው ባለው ግርፋት እየሞቱ መሆናቸው ተገለፀ፣





በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ተሰማርተው የሚገኙ ፖሊሶች እየተከተሉት ባለው ፀረ ህዝብ አካሄድ በነዋሪው ህብረተሰብ ላይ የተጠሉ በመሆናቸው ምክንያት፤ በላያቸው ላይ አንዳንድ ተበዳዮች እርምጃ ሲወሰድባቸው የሚረዳቸው ሰው ባለመምጣቱ የተናደዱት እነዚህ ፖሊሶች በአካባቢው ለሚኖሩ ንፁሃን ዜጎች እናንተ ገዳዮች ወይም ለገዳዮች ተባባሪዎች ናችሁ በማለት ካሰሯቸውና። በአሰቃቂ ሁኔታ እየገረፏቸው ባሉበት ባሁኑ ሰዓት አንዳንዶች ግርፋቱ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው እየሞቱ መሆናቸውን ምንጮቻችን  ከዞኑ አስታወቁ፣
  መረጃው አክሎ፦ እነዚህ ባልዋሉበት ወንጀል  እመኑ እየተባሉ እየወረደባቸው ባለው አሰቃቂ ምርመራ ምክንያት ከሞቱት ውስጥ አንዳርጋቸው ሙሉሰው የተባለ ግለሰብ በእስር-ቤት በወረደበት ከባድ ጉዳት ምክንያት ሊሞት ሲል ለቤተሰቦቹ አሞታል ኑ ውሰዱት በማለት ያስረከቧቸው ሲሆን፤ እሱ ግን ታሞ ሳይሆን ግርፋት እንደበዛበት መናገሩና፤  ብዙም ሳይቆይ መስከረም 18/2007 ዓ.ም እንደሞተ የገለፀው መረጃው፤ የመዋቹ ቤተሰብ የልጃችን ገዳዮች ፖሊሶች ስለሆኑ በህግ ፊት ቀርበው ይጠየቁልን በማለት ክስ ቢያቀርቡም ክሳቸውን ተቀብሎ የሚያጣራ አካል እንዳላገኙ ምንጮቻችን ከቦታው ገልፀዋል።