Thursday, January 1, 2015

በላዕላይ አድያቦ ወረዳ የሚገኙ የስርዓቱ ካድሬዎች በሚሊሻዎች መካከል ታማኝና የማይታመን የሚል ከፋፋይ አካሄድ እየተከተሉ በመሆናቸው የታጠቁ ሚሊሻዎች እርስ በራሳቸው እንዲጋጩ እያደረጓቸው መሆናቸውን ምንጮቻችን ከወረዳዋ አስታወቁ።




    በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ላዕላይ አድያቦ ወረዳ የሚገኙ አስተዳደሮችና የስርዓቱ ካድሬዎች የካቲት 11 እየቀረበ ስለመጣ በከባድ ሽርጉድ ላይ ተጠምደው እንደሚገኙ የገለፀው ይህ መረጃ ይህንን ለመተግበርም በምድረ ፈላሲ ቀበሌ ማን ቀድሞ በታዘዘው ቦታ ተሰማርቶ ዋለ ማንስ ወደ ኋላ ቀረ ለማወቅ ባካሄዱት ስብሰባ በዓዲ አስገዶምና ዓዲ ሓመዶ በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
    ምንጮቻችን እንደገለፁት የስርዓቱ ተላላኪ የሆኑ የዓዲ አስገዶም  ሚሊሻዎች የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር በማለት በአድ ሓመዶ የሚገኙ ሚልሻዎች የትህዴን ተባባሪ ስለሆኑ አናምናቸውም ትጥቃቸውን ማውረድ አለባቸው በማለት ስለገመገሟቸው የዓዲ ሓመዶ ታጣቂዎች ትጥቃችንን የሚገፈን አካል ይምጣ በማለት ለነበረው ስብሰባ ረግጠውት በመውጣታቸው ምክንያት  ስብሰባው ያለ ፍሬ የተበተነ ሲሆን የተነሳውን ግጭት ለማብረድ በሚል ከወረዳ የተላኩ ጥላሁንና ልዑል የተባሉ የህወሓት ካድሬዎች ሁለት ጊዜ ፈትነው ሊሳካላቸው እንዳልቻለና የተፈጠረው ግጭትም ተፋፍሞ እየቀጠለ መሆኑን ምንጮቻችን አክለው አስታውቀዋል።
   እየቀጠለ ባለው ግጭት ታፈረ መለስ የተባለ የዓዲ ሓመዶ ነዋሪ የሆነውን    ታጣቂ ትጥቁን እንደአስጣሉትና በአካባቢው የሚገኙ ወታደሮችም በዓዲ አስገዶም የሚገኙ ሚሊሻዎችን እየያዙ ወደ ፊት እየዘመቱ መሆናቸውን ለማዎቅ ተችሏል።
    ይህ በእንዲ እንዳለ በወረዳዋ የዕጉብ ቀበሌ፤ የታብር አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ሶስት ወንድማማቾችን የትህዴን አባላት ናችሁ በማለት አስረው እያሰቃዩዋቸው እንደሚገኙና ታስረው ከሚገኙትም አልጋ ግርማይ ወለየስ፤ አፈወርቅ ግርማይ ወለየስና ዲያቆኑ ወንድማቸው ሲሆን ይህ በንፁሃን ወገኖች ላይ እየተፈፀመ ያለው የስርዓቱ እኩይ ተግባር በባሰ መልኩ እየቀጠለ እንደሚገኝም ምንጮቻችን  በላኩልን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።