Friday, March 13, 2015

በህወሓት-ኢህአዴግ ስርዓት ስር የሴቶች እኩልነት አይረጋገጥም!!



    ባለፉት ተከታታይ የሃገራችን ገዢ ስርዓቶች የሴቶችን መብት የሚገልፅ በህገ-መንግስት የሰፈሩትን ቃል ከተራ ፅሁፍ ባለፈ ተግባር ላይ ሊገለፅ የማይችል የወረቅት ልሳን ብቻ እንደነበር ለማንኛውም የሃገራችን ታሪክ የሚያውቅ ዜጋ የተደበቀ አይደለም።
    በትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል ወቅትና አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄድ በነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ የሴቶች ድርብ ጭቆና መሰረት ተደርገው ሲገለፁ የነበሩትን ሃቆች መነሻቸው ተመሳሳይ ነው። ይኸውም በገዢዎች ይደርስባቸው የነበረና አሁንም ያለ አስከፊ ጭቆና ካልተወገደ የህብረተሰቡ ግማሽ ሃይልና አቅም ያለመጥቀም ስለሚሆን በሁሉም ስራዎቻችን እንቅፋት ያመጣል የሚልና ሌሎች ምክንያቶች በወቅቱ ይቀርቡ ነበር።
     ያለፈውን የትግራይ ህዝብ የጀግንነት ታሪክ ስንዘክር በርካታ አኩሪ ፍፃሜዎች ለመጥቀስ ይቻላል። የሴቶች አቅምና ተሳትፎ ባለፉት ስርአቶች ሲገለፅ። ልጅ ከማሳደግና ቤት ውስጥ ከሚሰሩ ስራዎች ባለፈ እምብዛም ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ የሚያመላክት አስተሳሰብ ተይዞ ለዘመናት ቢቆይም የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ግን የደርግን ስርአት ለመገርሰስ በተደረገው የአስራ ሰባት ዓመት መራራ የትጥቅ ትግል የሴቶቹ የትግል አስተዋፅኦና ብቃት በግልፅ የተንፀባረቀበት ታሪካዊ ምእራፍ ተከስቷል።
  እነዚህ! የደርግን ስርዓት በመቃወም በወቅቱ ሲታገል ከነበረው አጠቃላይ ሃይል 1/3 ኛውን ተሳትፎ የነበራቸው በሰራዊቱ ውስጥ የነበሩ አርበኞች ያላቸውን ተፈጥሮአዊ ችግሮች ተቋቁመው በእልህና በጀግንነት ከአቅማቸው በላይ ታግለው። የነበረውን ግዙፍ የጠላት ሃይል አስወግደዋል። ይሁን እንጂ ይዘውት የተነሱለት ዓላማና ራእይ በወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ምክንያት ተኮላሽቶ እንዲቀር ምክንያት ሆኗል።
    የህወሃት_ ኢህአዴግ መሪዎች ከትግሉ ወቅት ጀምረው በሴቶች እኩልነት ላይ የነበራቸው እምነትና እንቅስቃሴ ካለፉት ገዢዎች ምንም ዓይነት ልዩነት አልነበረውም። በ1979 ዓ/ም አካባቢ በትግሉ ውስጥ የነበሩትን ሴት አመራሮች የሴት የበላይነት ታሳያላችሁ ተብለው ሲገመገሙ በኋላም በ1980 ዓም ላይ ሁለተኛ ኮንፈረንስ እንዲያካሄዱ ተደርጎ በስብሰባው ላይ አንስታይነት ወይም/ፊመንስት/ አመለካከት ነበራቸው በሚል መሰረት የሌለው ፖለቲካዊ ቃል የትግል ወኔያቸውን እንዲዳከም ተደርጓል።
    በዚህም መሰረት ትግሉ ውስጥ የነበራቸውን ብዛትና የአቅም ተሳትፎ ግምት ውስጥ በማያስገባ ካላፉት አባቶቻቸው በወረሱት ኋላ ቀር ባህልና አመለካከት ምክንያት በዛን ቅውቅት ፖለቲካዊ አቅማቸው ከነበሩት አመራሮች የማይተናነስ አቅም ቢኖራቸውም ቀጣይ ይካሄድ በነበረው የድርጅቱ ጉባኤ ግን ለአመራር የሚታጩ ሴቶች አልነበሩም ለማለት ያስደፍራል።
    የወያኔ ኢህአዴግ አመራሮች ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላም በየአምስት አመቱ በሚያካሄዱዋቸው አስመሳይ ምርጫዎችም ሴቶች ወደ ፊት በማምጣትና የመሪነት ተሳትፎአቸው በማረጋገጥ ላይም የሴቶችን እኩልነት አስመልከተው ከሚናገሩት የሃሰት ዲስኩር ባለፈ በተግባር ላይ የሚገለፅ የሴቶች እኩልነትን የሚያረጋገጥ መርህ ተከትለው አያውቁም።
ምክንያቱም የሃገራችን ኢትዮጵያ ሴቶች ብስራ ቦታቸው፤ በትምህርት ቤትና ዕለታዊ ስራቸው በሚያከናውኑባቸው አከባቢዎች በፆታቸው ለሚያጋጥማቸው ከባድም ሆነ ቀላል ጉዳት በስልጣን ላይ ባለው ገዢ መንግስት የሚሽከረከር ነፃነት የሌለው የፍትሕ አካል ብግለሰብም ሆነ በብዱን በመሆን በእናቶቻችን፤ እህቶቻችንና ሚስቶቻችን በአጠቃላይ የሕብረተሰብ መሰረት በሆኑት ሴቶች  ተገቢው የሕግ ከለላ ባለማግኘታቸው ምክኒያት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት ሰብአዊ ክብራቸው ሊጠበቅ አልቻለም።
    ለማጠቃለል የኢሃአዴግ መሪዎች የህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ መብት በያዙበት ባሁኑ ግዜ በተለይ የሴቶችን እኩልነት ይረጋገጣል ብሎ ማሰብ የሚቻል ስላልሆነ የእኩልነትና የአንድነትን ፀር የሆነውን ስርዓት አስወግደን በተግባር የሚገለፅ የዴሞክራሲ ስርዓት ለማረጋገጥ በተለይ የሃገራችን ሴቶች ያለፉትን ጀግኒቶች ፈለግ በመከተል መብታቸውን ለማስከበር  ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ት.ዴ.ን / ጎን ተሰልፎው መታገል ይገባቸዋል።