Sunday, December 14, 2014

በብሄር ብሄረሰቦች በዓል የሚነግድ ስርአት!!



አገራችን ኢትዮጵያ ከ 80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ያሏት፤ የሃይማኖት መቻቻል የሰፈነባት እንዲሁም የሰላምና የመከባበር ተምሳሌት መሆኗን  በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍረው ይገኛሉ ብቻ ሳይሆን አሁንም ቢሆን ያለፈውን ታሪክ አንግቦ እየተጓዘ ያለውን ጀግና ህዝብ ያቀፈች አገር መሆኗ ይታወቃል።
    ይህ አስደናቂ ታሪክ ግን ካለፉት መሪዎችና አሁን ካሉት ፀረ ህዝብ ስርዓቶች የወረሰው ሳይሆን ከቅድመ አያቶቹ የተማረው ልዩ ተሰጥኦና አስደናቂ የአስተሳሰብ ችሎታ የተማረው እንደሆነ  ታሪክ ይነግረናል።
    ስለ አገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና እድገታቸውን አንስተን ለማየት ብንሞክር። ጥቂት ከሚባሉ የብሄር ማህበረሰብ ውጭ። አብዛኛውን ህዝብ ያቀፉ የብሄረሰቡ ክፍል ማንነታቸው ተረስተው ከእንስሳ በታች ሆነው ለአያሌ ዓመታት እንዲኖሩ መገደዳቸው፤ በቁጥር የማይናቁም ቢሆን በነበሩትና አሁንም ባሉት ፀረ ህዝብ ስርዓቶች ደብዛቸው እየጠፉ የብሄረሰብ ቋንቋዎች መኖራቸው የሚካድ አይደለም።
   የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት ለማስመሰል ሲል የኢትዮጵያን ህዝብ አደናግሮ የስልጣኑን አድሜ ለማስቀጠል ሲል ራሱ የሃገራችንን ብሄር ብሄረሰቦች መብት እያፈነና። ከድህነት በታች ሆነው መጨረሻ ወደ ማይገኝለት የችግር አረንቋ ውስጥ እንዲዘፈቁ ምክንያት ሆኖ እያለ የብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና ዋናው ተጠያቂዎች ያለፉት ስርአቶች እንደሆኑ፤ ባሁኑ ግዜ ከሌሎች ያገራችን ህዝቦች እኩል ታይተው ያገራቸው ሃብት ተጠቃሚዎች መሆን እንደቻሉ፤ በየክልላቸው ራሳቸው በመረጧቸው መሪዎች ለመተዳደር እንደበቁ ወ.ዘ.ተ አስመስሎ መናገሩ እጅግ የሚያሳፍርና የሚያስገርም ነው። ምክንያቱም መሬት ላይ ያለው ሃቅ ከእውነታው ጋር ፈፅሞ ስለማይገናኝ ስልጣን ላይ ያለው የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት እየፈጠረው ባለው ብሄረሰቦችን የማጋጨት ተግባር። ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ አያሌ ንፁሃን ወገኖች ህይወታቸውን  ሲያጡ። እስር ቤት ውስጥ ታስረው እየተሰቃዩና አገራቸውን ለቀው ስደትን የመረጡ ዜጎችም እጅግ በርካታ ናቸው።
    የብሄር ብሄረሰቦች መብት ክብረ-በዓሎች በማዘጋጀና ህዝቦች በበአሉ ተገኝተው እንዲጨፍሩና እስክስታ እንዲመቱ በማድረግ የሚረጋገጥ ሳይሆን ህዝቡ የሚያነሳቸውን መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች በተገቢ መንገድ ተቀብሎ የሚያስተናግድ ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ጭፈራና ሽለላ የህዝቡን መብትና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ይመልሳሉ ተብሎ አይጠበቅም።
    ባለፉት ሳምንታት በሰሜን ጎንደር የኢህአዴግ ባለስልጣኖች እየተከተሉት ባለው ብሄሮችን የማጋጨት ተግባር የቅማንት ብሄረሰብ በአካባቢያቸው ከሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆች እንዲጋጩ ተደርጓል። በዚህ ድርጊት ስሜት ውስጥ የገቡ የብሄረሰቡ ተወላጆችም እራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር እንችላለን የሚል ጥያቄ አንስተው ከስርአቱ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት በጭልጋና ትክል ድንጋይ አካባቢ እየተንቀሳቀሱ የነበሩትን ተሽከርካሪዎች በማስቆም ስራቸውን እንዳስተጓጎሏቸውና የአማራ ብሄር ተወላጅ በሆኑ አስተዳዳሪዎች ጫና እየደረሰብን ነው በማለት ወደ ሚመለከታቸው አካላት ብሶታቸውን አቅርበው ተገቢ መልስ ባለማግኘታቸው ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የስርአቱ ፖሊሶች በለኮሱት ግጭት 7 የብሄረሰቡ ተወላጆችና ሌሎች 3 ፖሊሶች እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።
    ይህ አስነዋሪ ድርጊት የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ማስጠበቅን የሚያሳይ ሳይሆን አሁንም በብሄር ብሄረሰባችን ላይ ሲደርስ የነበረውን የመብት ጥሰት በተጠናከረ መንገድ እየቀጠለ መሆኑን የሚያሳይ እውነታ ነው። ስለዚህ! ይህ በስርአቱ አስመሳይ የመብት አስከባሪነት ስም እየተነገደ በየአመቱ የሚካሄደውን በዓል ሸፍጥ መሆኑንን ተረድተን አሁንም በስርአቱ ላይ የተጠናከረ ትግል ማካሄድ ይገባናል።