የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ተፈጥሮ የሸለመችው የሰብዓዊ መብቶች ባለፀጋ
ነው። ማንኛውም ሰው ደግሞ ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በህይወት የመኖር፤የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው።
እነዚህን መብቶች
ለማስከበር ደግሞ በአለማችን ላይ ከፍተኛ ተጋድሎ እየተደረገ መጥቷል። ምክንያቱም በየአገሩ የሚገኙ አምባገነን መንግስታት የዜጎችን
ሰብዓዊ መብቶች በመንጠቅ ራሳቸው ተጠቃሚ ሌላው ዜጋ እንደ እንስሳት አገልጋያቸው እንዲሆን ለማድረግ፣ የሞት ሽረት ትግል እየተደረገ
መጥቶ ዛሬ በብዙሃኑ አሸናፊነት መሰረት የሰው ልጅ የሰብአዊ መብቶች ተከብረው የሚኖሩባት አለምን ለማየት ቢበቃም በአንዳንድ አገሮች
ግን አሁንም ቢሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በመስፋፋት ላይ ነው።
ይህ የመኖርና ያለመኖር ትንቅንቅ በአገራችን ኢትዮጵያም ለረጅም ዘመናት
በህዝቦቿና በመሪዎቿ መካከል እየተደረገ መጥቷል። እስካሁንም መፍትሔ አላገኘም። እንዲያውም ከአለፉት ማዕከላዊ መንግስታት በባሰ
ሁኔታ የኢትዮጵያውያን ዜጎች ሰብዓዊ መብት በጡት ነካሹ በወያኔ ኢህአዴግ አመራሮች ተነጥቆ የኢትዮጵያ ህዝብ በጭቆና ቀንበር በወያኔ
ሰርአት ስር በባርነት እየተገዛ ይገኛል።
ዛሬ በአገራችን በህይወት የመኖር መብት፤ አይከበርም። የአካል ደህንነትና
የነፃነት መብቶችን በአምባገነኑ የኢ.ህአዴ.ግ አገዛዝ ተነጥቀናል። ዜጎች ምንም ባልታወቀ ምክንያትና ያለህግ አገባብ ጭካኔ በተሞላበት
ዘግናኝ ሁኔታ ይረሸናሉ። በባለስልጣናት በሚሰጥ ኢ-ሰብዓዊ ትዕዛዝ ንፁሃን ዜጎች በአጋዚ ሃይሎች እየተገረፉ አካላቸው እየጎደለና
ክብርን በሚያዋርድ ምርመራና ቅጣት ለአካለ ስንኩልነት ብዙዎች ተዳርገዋል። የስነ ልቦና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ብዙዎች ለአንጎል
ዘገምተኛነት ተዳርገዋል።
ሰላማዊ ዜጎች
መብታችንን ብለው በመጠየቃቸው ብቻ ያልተገባ ስም እየተሰጣቸው እንዲሸማቀቁ በማድረግና ከህብረተሰቡ በመነጠል፤ ባልታወቀ ሁኔታ አግቶ
በመውሰድ አድራሻቸውን ማጥፋትና በሀሰት ክስ ሀሰተኛ ምስክሮች እንዲመሰክሩባቸው እየተደረገ ፍፁም ኢ-ፍትሃዊ በሆነ አገባብ ለእስራትና
ለስቃይ እየተዳረጉ ይገኛሉ።
በዚህ በቅርቡ ጊዜ የወያኔ ኢህአዴግ አመራሮች በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ
የፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋና እስራት እንዲሁም የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ መመልከት እንችላለን። ዜጎች ለማንኛውም ሰው የሚያስፈልገውን
በህይወት የመኖር መሰረታዊ ፍላጎቶችና የማህበራዊ አገልግሎት አውታሮችን እንዲሟሉላቸው በመጠየቃቸው ብቻ የኢህአዴግ መንግሰት በእነዚህ ንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የጥይት እሩምታ በመክፈት የዘር ማጥፋት ፍፃሜ
አካሂዷል።
ይህ ሁኔታም በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ጠንካራ መንፈስ በየአካባቢው ህዝባዊ
አመፅን ወለደ በኦሮሚያ፤ በአማራ፤ በኮንሶና በሌሎችም አካባቢዎች ህዝብ በአደባባይ ላይ ሰብዓዊ መብቶቹን ለማስከበር ከፍተኛ የህይወት
መስዋዕትነት ከፍሏል። ደሙንም ስለ ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ አፍስሷል። እንደውጤቱም አሁን በአገራችን ላይ የታወጀውን የሰርአት የስልጣን
እድሜ ማራዘሚያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ለወያኔያውያን ድንጋጤና አማራጭ የሌለው ከሞት አፋፍ ስር የመባነን
ምክንያት ሆኗል።
አሁን በአገራችን ሙሉ በሙሉ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶች ፍፁም አይከበሩም።
አገራችን በወያኔ/ኢህአዴግ ወታደራዊ አገዛዝ ስር ወድቃ በታሪካችን ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዜጎች ላይ ግድያ፤ አፈና፤ ማስፈራሪያ፤
ኢሰብአዊ ምርመራና ሌሎችም ለመናገር አሳፋሪ የሆኑ ድርጊቶች በንፁሃን ላይ እየተፈፀሙ ይገኛሉ።
የሚገርመው ነገር አሁንም ቢሆን የወያኔ ኢህአዴግ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ
ከማምጣት ይልቅ በአምባገነንነት ረግጦ በመያዝ የአገሪቱ ሰላም ወደነበረበት ተመልሷል ይለናል። እውነታው ግን ሰቆቃውና ኢ-ሰብዓዊ
ፍፃሜው እየባሰ በመሄዱ አጠቃላይ በአገራችን ህዝቦች ላይ ፍራቻ፤ ስጋት፤ ሰርቶ ለመብላት አለመቻልና ወጥቶ ለመግባት መጠራጠር እንጂ
ሰላምና እፎይታን አላገኘም።
ምክንያቱም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የአንዲት አገር ሰላም ሊሰፍን
የሚችለው፥ ህዝቦቿም የሰላሙ ተጠቃሚ የሚሆኑትና መረጋጋታቸውን የሚያጣጥሙት የሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ ብቻ እንጂ በአምባገነንነት
በማስፈራራት አይደለም። ስለዚህ የሰብዓዊ መብቶችን በመግፈፍ የአንድ አገር ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም።
No comments:
Post a Comment