Sunday, February 25, 2018

17ኛው ዓመት የድርጅታችን ትህዴን ምስረታ በዓል የካቲት 19 ምክንያት በማድረግ ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ



  የተከበራችሁ በሃገር ውስጥና በውጭ አገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦች፣
- የተከበራችሁ በሃገር ውስጥና በውጭ አገር የምትገኙ የትግላችን ደጋፊዎችና ወዳጆች፣
- የተከበራችሁ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ስትሉ መተክያ የሌላትን አንዲት ህይወታችሁን በመስጠት በጋለው ህዝባዊ ትግል ጎራ ተሰልፋችሁ በመዋደቅ ላይ የምትገኙ የትህዴን ታጋዮችና ተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ።
በመጀመርያ እንኳን 17ኛው ዓመት የድርጅታችን ... የምስረታ በዓል የካቲት 19 አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን።
ህዝባችን በወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ተክዶ መራራ ስቃይና መከራ እንዲያሳልፍ ሲገደድ፤ የሰማእታት እናቶች የሚረዳቸው አጥተው አንገታቸውን ደፍተው ማልቀስ ሲጀምሩ፤ በህዝባዊው ትግል ወቅት የተጎዱ ጀግኖች ታጋዮች በከፈሉት ዋጋ መኩራት ሲገባቸው እየተሸማቀቁ ወደ ልመና ሲሰማሩ፤ ህዝባችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተጥሶ እኛ የምንልህ ብቻ ስማ በሚል ፈሊጥ እንዳይናገር ተሸብቦ እንዲኖር ሲፈረድበት ነበር፣ እንዲህ ያለውን የአፈናና የጭቆና ተግባር ሊቋቋሙ ያልቻሉ ጀግኖች የህዝብ ልጆች መስዋእትነት ከፍለው እንደሻማ በመቅለጥ በጨላማ የሚገኘዉን ህዝባችንን ብርሃን እንዲሆኑት በማለም 17 ዓመታት በፊት ልክ በዚችው ቀን የትግሉን ችቦ ያቀጣጠሉት።
ይህን ዓላማ መነሻው ያደረገው ህዝባዊ ትግል ከግቡ ለማድረስም ድርጅታችን ባሳለፍናቸው 17 የትግል አመታት ለህዝብና ለሃገር ጥቅም ሲል ነፍጥ አንስቶ የኢህአዴግን ስርዓቱን በመፋለም መስዋእት እየከፈለ መጥቷል። ድርጅታችን ዛሬም ከትላንቱ በይበልጥ በመጠናከር አደረጃጀቱን በማሻሻልና ሁለንተናዊ አቋሙን በማሳደግ በስርዓቱ የሚሸረቡ ደባዎችን በመበጣጠስ የመላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጋሻና መከታ ለመሆን ትክክለኛውን መስመር በመያዝ የአምባገነኑን የኢህአዴግ ስርዓት እድሜ ለማሳጠር በትግል ላይ ይገኛል።
የምንገኝበት ወቅት የኢህአዴግ ስርዓት ለማይቀርለት ሞት በማጣጣር ላይ የሚገኝበት ወቅት ነው። በመሆኑም ክህዝቡ ጎን በመሰለፍ ከሁሉም ተቃዋሚዎች ጋር በመተባበር በገደል አፋፍ ላይ የሚገኘውን ስርዓት በፍጥነት ለማስወገድ ከማንኛውም ግዜ በላይ ወገባችንን ጠበቅ ኣድርገን ለመፋለም ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።
ህዝባችን ላለፉት 26 ዓመታት እኛ እናውቅልሃለን በሚል ጭፍን የወያኔ-ኢህአዴግ ስርዓት አካሄድ ታፍኖ፣ በህገ መንግስቱ የሰፈረው የዴሞክራሲ ፅንሰሃሳብ በተግባር ግን ከመቃብር በታች ሆኖ ያሳለፈበት ሁኔታ ነው ያለው። ገዥው ሰርዓት ነፃነቱን ለተቀማው ህዝብ አይንና ጀሮ ሆነው በየጊዜው ብቅ የሚሉትን ሚድያዎችና ግለሰቦችን እያስፈራራ፤ እያፈነና ብሎም ከነ ህዝባዊ አመለካከታቸው በየእስር ቤቱ እንዲበሰብሱ እያደረገ እስካሁን ዘልቋል።
አንድ አምባገነን ስርዓት የህዝቡን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማፈን መቀጠል እንደማይችል፤ የታፈነ የህዝብ ጥያቄ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚፈነዳና ወደ ማዕበል እንደሚቀየር ግዜ እራሱ እያረጋግጥልን ያለ ሃቅ ነው። በአሁኑ ሰአትም ህዝባችን ጦሩን ሰብቆ የወያኔ-ኢህአዴግን ስርዓት ለመገርሰስ በየአቅጣጫው እያካሄደው ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ማየቱ በቂ ነው።
ህዝባዊ ተቃውሞው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅትም የስርአቱ ከፍተኛ ኣመራሮችና ካድሬዎች እንደጅብ እርስበርሳቸው ሲበላሉ መታየት ጀምሯል። ኢህአዴግን ያቆሙት ኣራቱ ድርጅቶችና እህት ድርጅቶች በሚባሉት ቡድኖች መካከልም መናናቅ፤ አለመደማመጥ፤ ድርጅታዊ ነጻነት ያለመኖር፤ ግለኝንት፤ የስልጣን ስግብግብነትና ሌሎችም ችግሮች በመፈጠራቸው በማይወጡት አዘቅት ውስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ።
የወያኔ ኢህኣዴግ መሪዎች በተግባራችው ሳያፍሩ ኣሁንም "እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል" በሚል ኣስተሳሰብ ህዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸው ይመስል የሚመሩትን ክልል ህዝብ የመሰሪይ ተግባራችው መሳሪያ ለማድረግ ሲሉ ስለ ህዝቡ እየስሩና እየተከራከሩ እንደሆነ በመስበክ እነሱ በገቡበት የመሰነጣጠቅና የመበታተን ሴራ ውስጥ እንዲገባላቸው ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ክቡር የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፦
ባለፉት 26 ዓመታት ስርዓቱ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ሲጠቀምባቸው ከቆዩት ተንኮሎች አንዱ አንተን በአከባቢ፤ በብሄር፤ በሃይማኖት ወዘተ እያጋጨ በስልጣን ላይ መሰንበትን ነው። በዚህም ምክንያት በበርካታ የአገሪቱ አከባቢዎች ግጭት ሲካሄድ ቆይታል። እነዚህ ግጭቶች ስርአቱ ራሱ የፈጠራቸው ቢሆንም በሌላ አካል እንደተፈጠሩ በማስመሰልና ሌላውን በመወንጀል የችግሩ ፈቺ መስሎ እያምታታ ቆይቷል።
አሁንም ላለፉት ዓመታት በላይህ ላይ ሲፈጽመው የቆየውን ግፍና በደል ኣልበቃ ብሎት በአንድ ድምጽ በስርዓቱ ላይ እያካሄድከው ያለውን ተቃውሞ በማዳከም ነገ እንደ ህዝብ አንድ ሆነህ እንዳትቀጥል አንድነትህን በታትኖ ለመጥፋት እየሰራ ነው።
ስለዚህ ስርዓቱ ካዘጋጀልህ ወጥመድ በመውጣት በብሄርና በሃይማኖት ሳትለያይ ትላንትም ዛሬም ጠላትህ የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት መሆኑን አውቀህ አንድነትህን አጠናክረህ ስርዓቱን ለመጣል እያካሄድከው ያለውን ትግል በማጠናከር ሃገራችንን ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ ለማዳንና ወደማይቀረው ድል እንድትገሰግስ ... ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበራቹ የተቃዋሚ ድርጅቶች፦
የወያኔ-ኢህአዴግ ስርዓት እስካሁን ድረስ በስልጣን የቆየው የህዝብ ድጋፍ ኖሮት ሳይሆን የተቃዋሚው ሃይል የህዝብን ፍላጎትና ክብር ኣስቀድሞ የተበታተነውን የህዝብ ሃይል ወደ አንድ በማምጣት ህዝባዊ ትግሉን ማፋጠን ባለመቻሉ ነው። ያለንበት መድረክም ከማንኛውም ጊዜ በላይ ልዩነታችንን በማጥበብ ከህዝባችን ጎን የምንቆምበትና ሃገራችንን ከመበታተን አደጋ የምናድንበት ወቅት መሆኑ ትህዴን በፅናት ያምናል።
ስለዚህ አሁንም የተጀመሩትን የትብብር ስራዎች በማጠናከርና ወደፊት በማስኬድ ኣሁን ካለው በላይ ለመስራትና ትግላችን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በማድረስ ህዝባችንን ከስቃይ ለማውጣት በልበ ሙሉነት መስራት ይገባናል።
በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት በወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ምክንያት የተዳከመውን የህዝባችን አንድነት አጠናክረን በኢትዮጵያዊ መንፈስ እንዲታገል ማድረግና፣ በአገራችን የመከባበርና የመተጋገዝ መድረክ መፍጠር የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓትን ለመገርሰስ ከምናደርገው ትግል አንድ አካል መሆኑ ተገንዝበን ያለሰለሰ ጥረት እንድናደርግ ትህዴን ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበርክ ጀግና የትህዴን ታጋይ፦
ስለ ህዝብና ስለ ሀገር በበረሃ እየተንከራተትክ ከግላዊ ጥቅምና ፍላጎትህ ርቀህ እየከፈልክ ያለኸውን ወደር የለሽ መስዋእትነት የተከበረ ነው። በሰራሃቸው ስራዎችና ባሳየኸው ህዝባዊነትም በኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ገብተህ ትግላችን ተቀባይነት አግኝቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች እየተቀላቀሉት ይገኛሉ። ስለዚህ ኣሁንም የጀመርከውና መስዋእትነት የከፈልክለት የድርጅትህ ዓላማ ወደ ግብ ለማድረስ እውነተኛ ህዝባዊ መስመርህን ጠብቀህ እንድትቀጥል ድርጅትህ ያሳባል።
ድርጅታችን 17 ዓመታት በፊት በየካቲት 19/1993 / የጀመረው የትጥቅ ትግል ወቅታዊና ፍትሃዊ የነበረ መሆኑ ከምን ግዜም በላይ ኣሁን ሊረጋገጥ ችሏል። ኣሁንም ያለው ኣማራጭ የጀመርነውን ህዝባዊ ትግል ግቡ እንዲመታና የመላው ህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የትጥቅ ትግሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ... እያረጋገጠ፣
እንኳን 17ኛው ዓመት የድርጅታችን ትህዴን የምስረታ በዓል የካቲት19 አደረሰን አደረሳችሁ እያለ በድጋሚ መልካም ሞኞቱን ይገልጻል።
ክብርና ምስጋና እዚህ ላደረሱን ጀግኖች ሰማእታት!!
ድል ለጭቁኖች!!

No comments:

Post a Comment