Wednesday, September 10, 2014

አዲሱን የ2007 ዓ/ምና የቅዱስ ዮሃንስን በዓል በማስመልከት ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ!



  አገር ውስጥና ከአገር ውጭ ለሚገኘው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ለጀግናው ሰራዊታችን፤ ለድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች እንኳን ለአዲሱ ዓመት 2007’ና ለቅዱስ ዮሃንስ በዓል በሰላም አደራሳችሁ አደረሰን።
    የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት ስልጣን ላይ ከወጣበት ማግስት ጀምሮ አሁን እስካለንበት ሰአት ድረስ። በየአመቱ የሚገባቸውን ቃልና የዴሞክራሲ ባዶ ንግግሮች ተግባር ላይ ማዋል አልቻለም ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ ላይ ስልጣን እንደተቆጣጠረ ለማስመሰል እየተጠቀመበት የነበረውን የማደናገርያ ቃላት ሳይቀር ሙሉ በሙሉ በመካድ በህዝቡ ላይ መጠነ ሰፊ በደሎች እያደረሰ ይገኛል።
     የአገራችን ባለስልጣኖች ከፀረ ህዝብ ባህርያቸው በመነሳት ይዘውት ያለውን ስልጣን ተጠቅመው በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ እየፈፀሙና በሰላማዊ መንገድ ትግል ማካሄድ ይቻላል ብለው ለሃገርና ለህዝብ ጥቅም አስበው ተደራጅተው እየታገሉ ለሚገኙ ፖለቲካዊ ድርጅቶች የተለያዩ ፀረ ህዝብ አዋጆች እያወጡ በማፅደቅ ራሳቸውን የሰላም ሃዋርያ አድርገው በመቁጠር ለስርአቱ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ለፈረጇቸው ግለሰቦች አገር ለማፈራረስ የተነሱ፤ ያገር ልማት የማይፈልጉ፤ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ መንግስትን ሊገለብጡ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች በማለትና በላያቸው ላይ ከሃቅ የራቁ ውንጀላዎች በመለጠፍ ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች እያጉሯቸውና ደብዛቸው እያጠፏቸው ይገኛሉ።
     ስርአቱ ለሰላም እንደማደናገርያ እየተጠቀመ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ እያደረሰው ያለው ሰብአዊነት የጎደለው ጭፍጨፋ በሃይማኖት ላይም ጎልቶ እየታየ ያለውና ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የአፈና ተግባር መሆኑን፤ የመብት ጥያቄ ባስነሳው የሞስሊም ሃይማኖት ተከታይ በሆነው ማህበረሰብ ላይም እጁን በማስገባት አንድ ግዜ የውጭ እጅ ያለበት ሌላው ግዜ የሞስሊም መንግስት እንዲመሰርቱ ፍላጎት ያላቸው የሃይማኖት አክራሪዎች ናቸው በሚል መሰረተ ቢስ ውንጀላ ንፁሃን ዜጎቻችንን እያሰቃያቸው እንደሚገኝና በልማት ሰም አሳቦ ህዝቡ ባላመነበት መንገድ የመሬት ሽግሽግ በማድረግ። ካንዱ ቦታ አስነስቶ ወደ ሌላው አካባቢ አሳልፎ የመስጠት ጭፍን እርምጃ ባሁኑ ግዜ እየታየ ያለው የስርአቱ ብልሹ አስተዳደር መገለጫ ነው።
     የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት ባገራችን ላይ እንዲኖር የሚገባው መንግስት ሰፊውን ህዝብ በሚያካሂደው ነፃና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት መመረጥ አለበት ብሎ የሚናገር ቢሆንም። መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ እውነታ ግን በእጅጉ ከሃቅ የራቀ ነው።
     ባለፉት አመታት የተካሄዱትን አራት የምርጫ ሂደቶች በምን መልክ እንዳለፉና ምን አይነት ገፅታ እንደነበራቸው መላው ህዝባችን እንደሚያውቀውና አሁንም 2007 ዓ/ም እንዲካሄድ እየተፈለገ ያለው ከወዲሁ ሳይካሄድ ማን አሸናፊ እንደሚሆን በታወቀው አስመሳይ ምርጫ ላይ ሊያደናቅፉኝ ይችላሉ ብሎ ላሰባቸው ወገኖች ካለ ምንም ተጨባጭ ወንጀል ከወዲሁ እስር ቤት ውስጥ እያስገባቸው ይገኛል። ይህ ተግባርም ባገራችን ለማስመሰል እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ትግል እንደማይቻል ግልፅ ያደረገና በአንፃሩ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለውን የትጥቅ ትግል አማራጭ በተጠናከረ መንገድ እንድንቀጥልበት የሚያደርግ ነው።
 የተከበርህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ።-
      ስርአቱ ሆን ብሎ ህዝቡን ለማደናገርና ባዶ ተስፋዎች ለማሰነቅ፤ ካለ ኢህአዴግ ስርአት ሌላ መንግስት ልማት ማረጋገጥ ከቶ እንደማይችል፤ ምርጫ በሚቀራረብበት ወቅት እንደመንግስት ሊሰራቸው የሚገባውን ግንባታዎች በብዙሃን መገናኛ እያቀረበ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ መጠቀም፤ በቀጣይ ምርጫ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ለሚላቸው ድርጅቶችና ግለ ሰቦች ማዳከም፤ ማስፈራራትና ማሰር፤ ከምንጊዜውም በበለጠ በስርአቱ እየተሰራባቸው ያሉ ፀረ ህዝብ ተግባሮች ናቸው።
    አሁንም ባገር ውስጥና በውጭ የምትገኘው ህዝባችን በብሄርና በሃይማኖት ሳትለያይ አገራችን ከዚህ አፋኝ ስርአት ነጻ እንድትወጣና ዜጎች ባገራቸው ኮርተው እንዲኖሩና የሃብታቸው ተጠቃሚ ሊሆኑ ከተፈለገ አገር ውስጥ ይሁን ካገር ውጭ የምትገኘው ወገናችን ያለምንም ልዩነት ትግልህን በማጠናከር ስልጣን ላይ የሚገኘውን አምባገነን ስርአት ለማስወገድ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ት.ህ.ዴ.ን/ ጥሪውን ያቀርባል።
 ለአገራችን ተቃዋሚ ድርጅቶች።-
    ባሁኑ ሰዓት አገራችን ከመቼውም ግዜ በበለጠ ለውጥ በመሻት ላይ ትገኛለች ይህን ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ሁላችንም አገራዊ የሆነ አስተሳሰብ ይዘን ለውጥን ማምጣት የሚያስችል መንገድ ስንከተል ብቻ መሆኑን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ት.ህ.ዴ.ን/ ያምናል።
 ስለሆነም አስተሳስባችንና አቅማችንን ለትግሉ በማበርከት አንድነታችንን አጠናክረን ወደ ማይቅረው ድል እንድንጓዝ ትህዴን ጥሪውን እያቀረበ ዛሬም እንደወትረው በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ኣብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ይገልፃል።      
የተከበርህ ጀግናው ሰራዊታችን ።-
      ለሃገር ክብርና ነጻነት ብለህ እየከፈልከው ያለህው መስዋእትነትና ህዝቡ ሰላምና እድገት እንዲያገኝ በማለት እያካሄድከው ያለው ትግል ሁሌም የሚበረታታ አኩሪ ታሪክ ነው፣ ይህን የተቀደሰ ተግባርና አስተሳሰብ እንድትሰንቅ በመቻልህም ከፍተኛ ክብር ይገባሃል፣ ድርጅታችን ት.ህ.ዴ.ን አሁን ያለበትን የእድገት ደረጃ እንዲደርስ የቻለውም እላይ እንደተገለጸው ጠንካራ ብቃትና ህዝባዊ አስተሳሰብ አንግበህ መስዋእት በመክፈልህ ነውና አሁንም እያራመድከው ያለኸውን ህዝባዊ ትግል አጠናክረህ መቀጠል ይገባሃል እያልን አዲሱ አመት 2007 ዓ/ም የለውጥና የሰላም አመት እንዲሆንልን እንመኛለን።

  የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ  / ት.ህ.ዴ.ን /   
ጳጉሜን 5/2006 ዓ/ም  
ድል ለጭቁኖች!!