Monday, May 16, 2016

በኢህአዴግ የፍትህ ተቋማት የሚረጋገጥ የህግ የበላይነትን የለም!!



     በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የፍትህ ተቋማት።ህዝቦችን በግልፅነት የሚያገለግሉና የህዝቦችን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩ ከህግ ውጭ የሚራመድ ማንኛውንም አካል የመገሠፅና ተጠያቂ የማድረግ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው፣ ዋነኛ ተግባራቸውም አለማቀፋዊ የሆኑ የሰው ልጅ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር፤ በህግ የበላይነት የሚመራ እኩልነትና ፍትሃዊነት የሚከተል አስተዳደር እንዲፈጠር ማድረግ ነው።
    በአገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙትን የፍትህ ተቋማት ስንመለከት ግን መንግስት በየእለቱ የሚያወጣቸውን አምባገነናዊ አዋጆችና ትዕዛዞችን በመከተል በንፁሃን ዜጎች ላይ ወያኔ የሚያዝዛቸውን የእስራትና የሞት ፍርድ እየፈረዱ በዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ ግፍ እየፈፀሙ ይገኛሉ፣ ይህም እራሱ የወያኔ ሴረኛ ቡድን ይቃወሙኛል ብሎ የሚፈራቸውን የለውጥ ሰዎችና የዴሞክራሲ ጥያቄ ያነሱ ምሁራንን በእጅ አዙር ስሪት አሸባሪዎች ብሎ በማስፈረድ የኢትዮጵያን ብርቅየ ልጆች በአረመኔያዊ ተግባሩ እየመነጠራቸው ይገኛል።
    በአንፃሩ እነዚህ የፍትህ ተቋማት ተብየዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች፤ከፍተኛና መካከለኛ ፍርድ ቤቶች ፤አቃቢያነ ህግ እና ችሎት ሰሚዎች ኢህአዴግ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፅመውን ግፍና በደል  መመልከትም መጠየቅም አልቻሉም፣ የሥርዓቱ ባለስልጣናት የህዝብንና የሃገርን ሃብት እንደፈለጉት እየዘረፉ ቢሊየነር ለመሆን ሲሽቀዳደሙና ካዝናቸውን ሲሞሉ ህዝባችን በየአደባባዩ አቤቱታውን ቢያሰማም እንኳ አለሁ የሚለው ግን አላገኘም።
     ምክንያቱም ከፍትህ ሚኒስቴር ጀምሮ ከላይኛው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከታችኛው የፍትህ አካል ድረስ የተዘረጋው  መዋቅራዊ አስተዳደር በኢህአዴግ አምባገነናዊ አመራሮችና ስግብግብ ካድሬዎች የተጠፈጠፈ በመሆኑ ነው።
    መልካም አስተዳደርን የናፈቀው የኢትዮጵያ ህዝብ እስካሁን ድረስ ስሜቱን የሚያዳምጥለት የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያስከብርለትና በፍትህና በእኩልነት የሚዳኘው ስርዓትም ሆነ ህገ-መንግስታዊ አስተዳደር አላገኘም፣ ይልቁንስ ካለፉት ስርዓቶች በከፋ መልኩ ፀረ ህዝብ የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ቡድን ለ25 ዓመታት በፋሽስታዊ ተግባራቸው እያሰቃዩት ይገኛሉ።
    ኢህአዴግ የስልጣን ጊዜውን ለማስረዘም ሲል በየጊዜው የሚያወጣቸው የልማት ሳይሆን የጥፋት መርህ የሆኑት አዋጆቹን ሳይወዱ በግድ በፍትህ አካላት እንዲፈፀሙ ያደርጋል፣ ይሄንን የወያኔ አምባገነናዊ ትዕዛዝ ያልተቀበሉና የህግ የበላይነት እንዲከበር በሙያቸው የጠየቁ ቅኑ ዳኞችም ፍርድ አጓድለዋል ተብለው ግማሹ ወህኒ ቤት ሲወረወሩ የተቀሩት ስርአቱ በፖለቲካዊ መርዝ ዓይኑ የተመለከታችውንም የውሃ ሽታ አድርጓቸዋል።
        በህግ ባለሙያዎች የሚወጡትን ህጎች ኢህአዴግ ለራሱ በሚጥመው መንገድ ለአምባገነናዊነቱ ማሳኪያነት እንደመሰለው በመተርጎም ብዙ ወጣቶችን አሰቃይቶበታል። ብዙዎችንም ለስደት ዳርጎበታል።
        በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰብዓዊ መብቱ፤ ህገ መንግስታዊ ሉኣላዊነቱ የስልጣን ባለቤትነቱና በፍትህ የመዳኘት መብቱ አልተረጋገጠለትም፣ መልካም አስተዳደር አልሰፈነለትም፣ የህግ የበላይነት አልተረጋገጠለትም፣ እነዚህን ከባድ መንስኤዎች ተከትሎም በአገሪቱ ከጫፍ እስከጫፍ ተቃውሞዎች እየተቀጣጠሉ ብዙ ወጣቶች ቢቀጠፉም ትዕይንተ ህዝቡ ግን መፍትሄውን በክንዱ እስከሚያመጣ ድረስ በተጨቋኝነት ድምፅ ይቀጥላል።
     በአጠቃላይ ህዝብን በቀናነት ለማገልገልና ህግና የህግ የበላይነትን ለማስከበር።የተቋቋሙት የፍትህ ተቋማት የመንግስት ባለስልጣናት የሚፈፅሙትን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ፍፃሜና በዝባዥነታቸውን መርምሮ ተጠያቂ ባለማድረጉ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማንገብገቡን ቀጥሏል።
     ስለዚህ ለዚህ በመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ያማቖቑት ህዝብ በዚህ ሳምንት የፍትሕ ሳምንት ተብሎ በአገር ደረጃ በሚድያዎቻቸው ቀርበው የተለመደዉን ኢህአዴጋውዊ የመደናገር ባህሪያቸው በህዝባችን ላይ ነጋ ጠባ የሚቀልዱበት እድል ልንሰጣቸው አይገባም።






No comments:

Post a Comment