Friday, March 16, 2018

በሞያሌ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በስህተት ነው በሚል በኮማንድ ፖስቱ የተሰጠውን መግለጫ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ። በሞያሌ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ሲልም ጠንካራ አቋም ይዟል።



በክልሉ ፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ እንደተናገሩት የተፈጸመው ግድያ በስህተት እንዳልሆነ መረጃ አለ። ድርጊቱን የፈጸሙት ብቻ ሳይሆኑ የመከላከያና የኮማንድ ፖስቱ አዛዦች ጭምር በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል አቶ ታዬ ደንደአ።
  የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቄሮዎች ላይ ምርመራ መጀመሩን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሀሰት መሆኑን በመግለጽ ምርመራ ካስፈለገም የፌደራል ፖሊስ ምን አገባው የሚል አቋም መያዙ የሚታወስ ነው። ሰሞኑን በሞያሌ የተከሰተውን ዕልቂት በተመለከተ የኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት የሰጡትን ምላሽ እንደተለመደው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ውድቅ አድርጎታል።
  የሴክሪተርያቱ ተወካይ ሌ/ጄ ሀሰን ኢብራሂም ከ10 በላይ ሰዎች በግፍ ለተጨፈጨፉበት ድርጊት በሰጡት መግለጫ ጉዳዩ በስህተት የተከሰተ ነው። እርምጃም እንወስዳለን ማለታቸው ከፍተኛ ቁጣን አስከትሏል። የአገዛዙን መግለጫ በይፋ በመቃወምም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አቋሙን ገልጿል።
  የተፈጸመው በስህተት አለመሆኑን እናምናለን ያሉት የኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ አንዳንዶቹ ተንበርከኩ ተብለው ግድያ እንድተፈጸመባቸው ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ገልጸዋል። ለሞያሌው ጭፍጨፋ ተጠያቂዎቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ብቻ እንዳልሆኑም አቶ ታዬ ጠቅሰዋል። ትዕዛዝ ያስተላለፉት የኮማንድ ፖስት ሃላፊዎችና የመከላከያ አዛዦችም በህግ ሊጠየቁ ይገባል በማለት ገልጸዋል።

 

No comments:

Post a Comment