በሃገራችን በወያኔ ኢህአዴግ ከፋፋይ ስርዓት ምክንያት ብሄር ብሄረሰቦች ራስ በራሳቸው በመጥፎ አይን እየተያዩ
አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ቤንሻንጉል ወዘተ እየተባባሉ በመከፋፈል ላይ ባሉበት ግዜ ገዢው ስርዓት ኢህኣዴግ ግን ውስጡን ሳያፀዳ ከውጭ
ሃገሮች ጋር ጥሩ ዲፕሎማስያዊ ግኑኝነት አለን እያለ መወትወት እንደ ዋና ስራ ቆጥሮ ሰፊ የሚድያ ሽፋን ሰጥቶ እየተናገረለት ይገኛል፣፣
ህዝባችን በዴሞክራሲና በፍትህ እጦት
ምክንያት ጎዳና ላይ ወጥቶ ሰለማዊ ሰልፍ ሲያደርግ ስርአቱ ተላላኪዎቹን ተጠቅሞ በእሩምታ ተኩስ እየፈጀ ባለበት ግዜ በሃገራቸው
ሰላምና ዴሞክራሲ ሰፍኖ በተረጋጋ ህይወት ካሉት ሃገሮች ጋር ዲፕሎማስያዊ ግኑኝነት መስርተናል እያለ መናገሩ ለማንም ኢትዮጵያዊ
ወገን የሚያሳዝን ነው፣፣
ህዝቡ በየአመቱ በችግር እየተጠቃ የወያኔ
ኢህኣዴግ ስርዓት ደግሞ ለውጭ አገሮች እርዱኝ እያለ እጁን ዘርግቶ የነጮች እጅ እየጠበቀ የሚኖርና በተጠዋሪነት በሽታ የሚሰቃይ
መንግስት በመሆኑ፣ ለዚህ የምፅወታ ዝምድና ግን ጥሩ ዲፕሎማሲ አለን ከማለት እርዳታ የሚሰጡኝ ደንበኞች አሉኝ ቢል ታማኝነት ባተረፈ
ነበር፣ ትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነድፎ በትጋት እየሰራ ህዝብ ከተጠዋሪነት ለማውጣት ጥረት ማድረግ እየተገባው የልመና መረቦች እየዘረጋ
ይገኛል፣፣
እንደ ኢህአዴጋውያን አስተሳሰብ ዲፕሎማሲ
ማለት መሬት ለባዕድ መሸጥ ማለት ነው፣ በዚህ ሃላፍነት የጎደለው ስትራቴጂ ደግሞ ቁጥራቸው የላቀ የአገራችን ወጣቶች የእርሻ መሬት
የሌላቸው ትዳር ይዘው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተጠግተው የሚኖሩ እያሉ በሺዎች ሄክታር የሚያክል ድንግል መሬታችን ለአንድ ክፍለ ዘመን
ያክል ለህንድ፤ቻይና፤ሳውዲ ኣረብያና ለሌሎች ሃገሮች በእርካሽ ዋጋ እየሸጡ ለም መሬታችን ያፈራውን ወደ ውጭ ተጭኖ እየሄደ ተጠቃሚዎች
መሆን እየተገባን ታዛቢዎች ሁነን እየኖርን ነው፣፣
መዋእለ ነዋያቸው ሊያፈሱ የሚችሉ ዜጎቻችን
እድል ተንፍገው ለአንዳንዶቹ ደግሞ ተመጣጣኝ ያልሆነ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ግብር እንዲከፍሉ እየተገደዱ ለኪሳራ ተዳርገው የስራ
ተቋማቸውን እየዘጉ፤ ግብር አልከፈላችሁም ተብለው ወደ እስርቤት እየታጎሩ ባሉበት ግዜ “ለቤት እመቤቷን ገረድ አስወጣቻት” እንደሚለው የትግርኛ ኣባባል ከውጭ ሃገር
ኢንቨስተሮች እያመጡ ሃገራችን ሞልተዋት ይገኛሉ፣ እነዚህ ከሀሃዲ አመራር ነን ባዮች ይህን ዲፕሎማሲ ብሎ የሚጠሩት ለህዝባቸው ማገልገል
እየተገባቸው የውጭ ሃገሮች አሽከር መሆናቸው ነው፣፣
የወያኔ ኢህኣዴግ አመራሮች አመሪካ ውለን
መጣን፤ኣውሮፓ አድረን መጣን ቢሉን በህዝባችን ላይ ያለው ፋይዳ ምንድ ነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ “ምንም”
ይሆናል፣ ለውጥ መምጣት የሚችል የህብረተሰቡ ኑሮው ለመቀየር ቢሞክሩ
ነው፣፣
በወያኔ-ኢህአዴግ መጥፎ አስተዳደርና የኑሮ
ችግር ምክንያት ህዝባችን ወደ አረብ አገሮች ተሰዶ ኑሮውን ለመግፋት በማሰብ ሃገሩን ለቆ ሲወጣ እነዚያ የሚሰደድባቸው ሃገሮች በዜጎቻችን
ላይ በጅምላ የመግደልና የማሰር እርምጃ በሚወስዱባቸው ግዜ የኢትዮጵያ መንግስት ፅኑ ዲፕሎማስያዊ ግንኙነት ቢኖረው ኑሮ በሃገሮቹ ውስጥ የሚገኙ ኢምባሲዎችና
ቆንስላዎች ለዜጎቻቸው ጠበቃ የማይቆሙበት ምክንያት የለም፣፣
ቁጥራቸው የላቀ ዜጎቻችን በአረብ ሃገሮች
ሲገደሉ የኔ ዜጋ ናቸው ብሎ የሚቆረቆር መንግስት አጥተው ደመ ከልብ ሁነው የቀሩ አሉ፣ በሞቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለብዙ አመት
ሸቅለው የሰበሰቡትን ንብረታቸው ተነጥቀው በመባረራቸው ላልተፈለገ ችግር ስዳረጉ በርካታ ደግሞ ለኣመታት ብእስርቤት ተጉሮው ይገኛሉ፣፣
ዲፕሎማሲ የሚባል እኮ በካሜራ እየቀረፅክ
ከአገር ወደ አገር እየተዘዋወርክ በስክሪን መታየት ብቻ ሳይሆን ለህዝብና ለአገር የሚረባ ተጨባጭ ስራ ወይም ደግሞ በኑሮና በሰላም
የሚታይ ለውጥ መኖር አለበት፣ እነዚ መሪ ነን ባዮች የቀን ሃሳባቸውና የሌሊት ቅዠታቸው ሁሉ እንዴት አድርገን ወደ የግል ካዝናችን
ዶላር እንሙላ የሚል ብቻ እንጂ እንዴት አድርገን ህዝብን የአገሩ ሃብት ተጠቃሚ እናደርገዋለን የሚል ሃሳብ አይታይባችውም፣፣
ለማጠቃለል እኛ ኢትዮጵያውያን ውስጣችን
እየታመስን እያለን ሰላም አለ ተብሎ ቢወራልን፤ የውስጣችን ፖአቲካዊና ማሕበራዊ ቀውስ ሳይረጋጋ የውጭ ዲፕሎማሲ አለን ቢሉን ለኛ
ለጭቁኖች ምንም ፋይዳ የለውም፣ ስለዚህ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ሳንታለል የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል
ስልጣኑ ተሽሮ ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈናት ኢትዮጵያ ለመመስረት መረባረብ ይገባናል፣፣