Saturday, July 5, 2014

ግሎባል መንደር በግሎባል አስተሳሰብ እንጂ በጎጠኝነት አይመሰረትም



    ግሎባል መንደር ስንል የአንድን ህብረተሰብ የብሄር፤የየቋንቋ የባህል፤ የሃይማኖት፤ የፖለቲካና የፍልስፍና አስተሳሰብ ልዩነቶችን ሳይገድቡት አብሮ የመኖር፤ የመደጋገፍና የመፈቃቀር ፍላጎት የሚያሳይበት ማለት ነው፣፣
     አሁን ባለንበት ዘመን ሆነን ያለፉትን ግዜያትና ዘመናት ስንቃኝ ብዙ የሚያሳፍር የታሪክ ክስተቶች በሃገራችንና በአለማችን ተፈፅመዋል፣ ባለፉት ዘመናት የሰው ልጅ ባለመንቃቱና ባለመማሩ ምክንያት በጣም የሚዘገንኑ ድርጊቶችና ክስተቶች ታይተዋል፣፣
     እነሱም በብሄር፤ በቋንቋና በሃይማኖት ልይነቶች የአለም ህዝብ ወደ ጦርነት ገብቶ ቡዙ የሰውና የንብረት ውድመት እንደተከሰተ የቅርብ ዘመን ትውስታችን ነው፣ ለምሳሌ በ16ኛው ክ/ዘመን በኢትዮጵያ የታየው በግራኝ መሓመድና በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የነበረው የመስቀል ጦርነት፤ ጀርመኖች በእስራኤሎች ያደረጉት የዘር ጭፍጨፋ፤ በ1986 ዓ/ም በርዋንዳ የታየው በቱቱሲና ሁቱ ዘር የማጥፋት ውድመትና በ1980ዎቹ በኮትዲቫር በክርስትያኖችና በእስላሞች የታየው ግጭትና ሌሎችም የምናስታውሳቸው ሃቆች ናቸው፣፣
     ስለሆነም አሁን ባለንበት 21ኛ ክ/ዘመን ከነዚህ ግጭቶች ተምረንና አስተካክለን አለማችን አሁን ወዳለችበት የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እውነታዎች መቀላቀል እንዳለብን ግድ የሚያሰኝ ሰለሆነ ከግሎባላይዘሽን አይን ሲታይም የጎጥ፤ ከባቢያዊና ክልላዊ ልዩነቶችን ትርጉም የሌላቸው እጅግ ኋላ ቀር አስተሳሰብ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፣፣
      የአለም ማህበረሰብ ከኋላ ቀር አስተሳሰብ ወጥቶ ብሎም የግሎባላይዘሽን ፈተና ለመወጣት በጋራ ካልቀዘፈ በስተቀር ተያይዘን በጋራ እንደምንሰምጥ የታወቀ ነው፣ ሆኖም ግን በአሁኑ ግዜ የወያኔ አሸባሪ ስርአት የኢትዮጵያን ህዝብ በብሄር፤ በጎሳና በሃይማኖት ለያይቶ አንድን ህዝብ ከሌላው ህዝብ እያናቆረና በጠላትነት አይን እንዲተያዩ እያደረጋቸው ይገኛል፣፣
      ለዚህም ስራው የወያኔ ካድሬ በመንግስት ደረጃ ሲሸለምበትና ሲከበርበት በቤተሰቡንም ውስጥ የኑሮ ደረጃው ከፍ ያለበት እንዲሁም ሰርግና ምላሽ የሆነበት ሁኔታ እንዳለ ለማንም ግልፅ ነው፣ አንድን ህብረተሰብ እያጣላህና በጠላትነት አይን እንዲተያዩ ማድረግ ይቻል ይሆናል ነገር ግን ትናንት ሃገራችን ለነበረችበት አሳዛኝ ሁኔታ በዘመኑ የነበሩ የፖለቲካ ሊሂቃን  ( ሙሁራን ) እንዲሁም የሽብር ማሃንዲስች ተጠያቂዎች እንደነበሩ ሁሉ አሁንም እንደዚያ እንደሚሆኑ “ ሃገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው ” ይህ ሲባል ትናንት ለህዝብና ለሃገር የበደሉትን ሰዎች ዘብጥያቸው እንደገቡ ሁሉ አሁንም የማይቀርላቸው እዳ መሆኑ ሊያውቁት ይገባቸዋል ምክንያቱም በሰፈሩት ቁና መሰፈር የማይቀር ነውና፣፣
     የዲሞክራሲ መብቶችና የነፃነት መብቶች መከበር ከተራው የሃገራችን ዜጋ መብት የሚጀመር ቢሆንም’ኮ እነዚህ መብቶች ለማስከበር በዋነኝነት ከፖለቲካ ፅናት የሚነሳ መሆኑን መታወቅ ያለበት ዋነኛ ጉዳይ ነው፣፣
     ይህ እንዳለ ሁኖ ሃገራችን ኢትዮጵያ በዋነኝነት በፖለቲካ መስኩ የግሎባል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆንና ህዝቦችዋ ከድንቁርና ከድህነት አረንቋ ወጥተው ወደ ተሻሉ የተባሉ ሃገሮች ተርታ እንድትሰለፍ መሟላት ያለባቸው ዘርፎች የዴሞክራሲ ስርአት መገንባት፤ ነፃ የሆነ የፍትህና የህግ አስፈፃሚ አካላት መኖር፤ የሰላምና መረጋጋት መኖር፤ የሰው ጉልበት፤ መሬትና ካፒታል የመሳሰሉ ለእድገታችን ወሳኝ የምንላቸው ሰለሆኑ እነዚህ በሃገሪቱ ውስጥ በነፃ ያለ ምንም የፓርቲ ወይም የካድሬ ጣልቃ ገቢነት መንቀሳቀስ ሲችሉና የግሎባል አስተሳሰብ ሲጎለብት እንጂ በጎጠኝነት አስተሳሰብ የሚመጣ አይደለም፣፣
     ይህ ለማድረግ ደግሞ ህዝብ ብቻውን መንቀሳቀሱ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ነፃነት ማስከበር እንኳ ቢችልም ህግ ካልደገፈው ግን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ መብት ሊጠበቅ ስለማይችል ተራው ህዝብ ባገኘው አጋጣሚ በመንግስት ህግ ላይ ተፅእኖ ማሳደር ካልቻለ መንገዱ ቀና ሊሆን አይችልም፣፣
     በመጨረሻም እኛ ኢትዮጵያዊያን የቦታ፤ የብሄር፤ የሃይማኖት ልይነቶች ሳይገድቡን ተፈቃቅረንና ተመካክረን ለኢትዮጵያ ሃገራችን አለኝታ እንድንሆንላት ከታሪካዊ ሃላፊነትም ጭምር ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ መስራት ይጠበቅብናል፣፣