Saturday, December 27, 2014

አገራዊ ምርጫ ሲቀራረብ የህዝቡ ችግር በባሰ ይጠነክራል!



   የኢትዮጵያ ህዝብ ለረጅም አመታት በተለያዩ ገዢዎች ስር ሆኖ ያሳለፋቸው አስከፊ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች አሁን  የምናያቸው ኋላ ቀርነትና ዘርፈ ብዙ አስከፊ ችግሮች ዋናው ምንጩና መሰረቱ ነው።
   ያገራችን ህዝቦች በየግዜው በላያቸው ላይ ሲደርሳቸው ከነበረው ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና፤ ግፍ፤ ስደትና መከራ ለመላቀቅ  ብለው በገዢዎቹ ላይ ያካሄዱትን መራራ ትግልና  የህይወት መስዋእትነት ከፍሎ ጠላቶቹን ቢያንበርክክም የእድል ጉዳይ ሆኖ ግን ስልጣን ላይ ያለው ፀረ ህዝብ ስርአት ሁሉንም ነገር ወደ ጎን በመተው በራሱ ጥቅም አዙሪት ብቻ እየተሽከረከረ በፊት ከነበሩ አምባ ገነናዊ ተግባሮች በከፋ መልኩ ወደ ባሰ መንገድ አሸጋግሮታል።
    የዚሁ ስርአት ብልሹ አካሄድና ዓፋኝ ተግባሮች ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባይሆንም በተለይ ባሁኑ ሰአት አስመሳይ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት በመላው ያገራችን ክፍል እየተፈጸሙ ካሉ በደሎች ጥቂቶቹን ለመግለፅ ያህል።
*   ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በሻንቦና ነቀምት ከተማ ውስጥ የሚኖር ህዝብ በኦሆዴድ ኢህአዴግ ላይ ያለውን ጥላቻ ከተቃዋሚዎች ተባብሮ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባዎች እንዳያካሂድ በስርአቱ መታገዱን ተክትሎ ህዝቡ በተቃዋሚዎች የተበተነውን ፓምፕሌት ይዘታቸውን አንብቦ በመረዳት አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን በማለት ሞራላዊ ድጋፉን መስጠቱ፤   
*   በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች በተለይ በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን የሚገኘውን ህዝብ በስርአቱ የፖሊስና የደህንነት አባላት ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነፃ ሆነው እያሉ የህወሃት አባላት ስላልሆኑ ብቻ የትጥቅ ትግል ከሚያካሂደው ትህዴን ጋር ስለምትተባበሩ ነው በምናካሂደው ስብሰባ ላይ የማትሳተፉት በማለት በተለየ ሁኔታ እያሰቃዩዋቸው እንደሆኑና ንፁሃን ወገኖችን አስረው  ትህዴን ጋር እየተባበርን ነበርን ብላችሁ በህዝቡ ፊት ተናገሩ ብለው በላያቸው ላይ ስቃይ  ቢያደርሱባቸውም የነዚህ ተበዳዮች መልስ ግን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ አባሎች ስላልሆን አንናገርም የሚል መልስ መስጠታቸው፤
*   በአፋርና ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙና ለረጅም ግዜ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ሲነታረኩ የቆዩትን የሁለቱም ህዝብ ወገኖች የኢህአዴግ ስርአት ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድና የክልሎቹ ህዝብ በማያምኑበት መንገድ ገዳማይቱ፤ ዕንድሮና ዓዳይቶ የተባሉት በዒሳ ጎሳ ተይዞ የቆየውን አካባቢ ወደ አፋር ክልል መወሰኑ በአፋር ክልል አጥቶት የነበረውን ህዝባዊ ተቀባይነት ለማጠናከር ታስቦ የተደረገ መላ ነው በሚል በሁለቱም ህዝቦች  መካከል እስከ ደም መፋሰስ ግጭት መድረሱ፤
*   በአ/ አበባ ከተማ ውስጥ ስርአቱን በመቃወም የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ ህዳር 28/2007 ዓ/ም በርካታ ንፁሃን ወገኖች በፌድራል ፖሊስ መታሰራቸውና የመታሰራቸው ምክንያትም በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በፌስ ቡክና ሌሎች ድህረ ገፆች ግንቦት 7 እንዲያቀነባብረው እናንተ እዚህ ሆናችሁ ስለ ምትተባበሯቸው ነው በሚል ምክንያት እንደሆነና። ነገር ግን  ሓቁ  በሰማያዊ ፓርቲ የተዘጋጀ መሆኑ፤
*   በትግራይና በአማራ መካከል የሚገኘው ግጨው፤ ማርዘነብን ማይ እንጓን በተባለው አካባቢ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ግጭቶች እየተከሰቱ መቆየታቸውና ይህን በህዝቡ ውስጥ የቆየውን ግጭት ለመፍታት ብለው ወደ ቦታው የተንቀሳቀሱ ባለስልጣኖች ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት እንዳላገኘ፤ በዚህ ጉዳይ የተነሳም ቀደም ሲል በፌደራል ፖሊስና ባካባቢው አርሶ አደሮች በተነሳው ግጭት የፖሊስ አባላት እንደተገደሉና አሁንም ቢሆን የተሰጠውን ፍትሃዊነት የሌለው ውሳኔ ህዝቡ ስላልተቀበለው እናንተ እኛን ልታስታርቁ ሳይሆን ይባሱን ልታጋጩን ነው የመጣችሁት በሚል የማግባቢያ ኃሳቡን እንዳልተቀበሉት በባህሪ ዳር ከተማ በህዝባችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ወ.ዘ.ተ… ባገራችን ውስጥ እየተፈጸሙ ከሚገኙ የመልካም አስተዳደር እጦት መነሻ ያደረገ አስመሳይ ሃገራዊ ምርጫ እየተቀራረበ ባለበት ግዜ በህዝቡ ላይ እየደረሱ ካሉት መጠነ ሰፊ ችግሮች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
    የወያኔ ኢህአዴግ ስርአት የምርጫው ቀን በሚቀራረብበት ሰአት ህዝቡንና የአለምን ማህበረሰብ ለማዛባት ሲባል ተግባር ላይ የማይውሉ መሰሪ ቃሎች እየተጠቀመ መምጣቱ ባለፉት 4 ምርጫዎች ተስተውሏል። እንደመንግስት መስራት የሚገባውን መሰረተ ልማቶች በምርጫ ዋዜማ ላይ እንዲታዩና ለፖሮፖጋንዳ ፍጆታ እንዲውሉ እያደረገ መቆየቱና አሁንም ቢሆን ይህንኑ ተግባር በሰፊው እየተጠቀመበት መሆኑን፤ በተለይ ከላይ ለመግለፅ  እንደሞከርነው የአንድ አካባቢ ህዝብ ለመያዝ ተብሎ ሌላኛውን በሚበድል መንገድ የሚካሄደው ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራር  ህዝብን እያስተዳደርኩ ነኝ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ አይደለም።
    ስለዚህ! ይህ ስርዓት እያራመደው የሚገኘው አጠቃላይ እንቅስቃሴ የስልጣኑን እድሜ የሚያራዝምበት የሂሳብ ስሌት ውስጥ በመግባት እንጅ የህዝቡን ጥቅም መነሻ በማድረግ እንዳልሆነ ተረድተን በህዝቡ እየደረሰ ያለውን ተደራራቢ ችግር ከወዲሁ በማስተዋል እንዲካሄድ በታሰበው አስምሳይ ምርጫ ላይ ተቃውሟችንን ማጠናከር ይገባናል።