Friday, January 30, 2015

የህወሃት 40ኛው የልደት በዓል አላማውና የተንኮል ዝግጅቱ!




     የህወሃት መሪዎች በአሁኑ ግዜ በትግራይ ህዝብ ዘንድ የነበራቸውን አመኔታ ጭራሽ ተሟጦና ተጠልተው እንደምራቅ የተተፉበት ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ እያዘጋጁት ባለው በዓል ላይ  ማለቂያ የሌላቸውን የውሸት ድርሳናት ፅፈው ህዝቡን በፎቶግራፍ፤ በፊልም፤ በግብዣና በዲስኩር በማደንዘዝ የህብረተሰቡን አቅጣጫ ቀይረው የስልጣን እድሜያቸውን ለማራዘምና እንደልማዳቸው የትግራይን ህዝብ እንደመጠቀሚያ ለማድረግ የታሰበ መሰሪ ተግባር መሆኑን ማንም ዜጋ የሚስተው አይደለም።
   ይህ ብቻም አይደለም 2007 ዓ/ም ላይ የሚደረገው አስመሳይ አገራዊ ምርጫ አስመልክተው የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ የህዝቡን አስተሳሰብ ለመቀየርና በተለይ የውሸት ታሪክ በመደርደር ወጣቱን ሃይል በአጉል የተስፋ መንገድ ከጎናቸው እንዲሰለፍ ለማድረግ አስበው እያደረጉት ያለ የከሰረ ብልሓትም ነው።
    የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግ ስርዓት ማስወገድ ብቻ ብቸኛው መፍትሄ ይመስለው ነበር እንጂ የካቲት 11 ገዢዎችን ነቅላ ሌሎች ፀረ ህዝብ ገዢዎች ታመጣለች ብሎ ኣስቦ አያቅም፣ ዳሩ ግን! ይኼ ሆኖ ቀረ።
    የካቲት ዓስራ አንድ የህዝቡን አደራ ማስከበር አልቻለችም ብሎ የተቃወመው ህዝብ እንዲታሰርና አገር ለቆ እንዲሰደድ ተደርጓል፣ እንደ ህዝቡ አነጋገር! ያ ሁሉ ወጣት ለየካቲት 11 ክብር ብሎ መስዋእት ከከፈለ በኃላ አዲሶቹ ገዢዎች ስልጣኑን መቆጣጠራቸው የትግላችን መጨረሻ ደመ ከልብ ሆነ ቀረ ብቻ ሳይሆን ልጆቻችን ከመስጠትና መስዋእትነት ከመክፈል ባለፈ ያገኘነው አንዳችም ጥቅም የለም በማለት የካቲት 11ይህን ሁሉ ወጣት በልታ ለጥቂት የገዢ መደብ ልጆች ጥቅም መቆሟ የበደል በደል ነው እያሉ ቃላቸውን እያሰሙ ያሉበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
   የህዝቡ ተስፋ የየካቲት 11 40ኛው ዓመት ሲከበር ከደርግ መንግስት የዜሮ ዴሞክራሲ ድምር ወጥተን በራሳችን ፈቃድ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላውነት ተከብሮ እርስ በርሳችን ተፋቃቅረን እንኖራለን የሚል ሃሳብ ነበር። ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በህወኃት መሪዎች ምክንያት ህዝቡ እርስ በርሱ በጥርጣሬ አይን እንዲተያይና በፈለገው ያገሪቱ አካባቢ ሄዶና ሰርቶ ማህበራዊ ንሮውን እንዳይመራ ሰብአዊ መብቱን በማፈን ራስ በራሱ እንደጠላት እንዲናቆር ፈርደውታል።
   ለማጠቃለል የደርግ ስርዓት የዜጎችን የመደራጀት፤ የመናገር፤ የመፃፍና ሌሎችም መብት የከለከለ መንግስት ስለ ነበር በወቅቱ የነበረው ወጣት የየካቲትን ጥሪ በመቀበል ታጥቆ ደርግን ለመደምሰስ ቢበቃም የመጨረሻ ውጤቱ ግን ለጥቂት አለቅላቂ ፀረ ህዝብ መሪዎች ብቻ ሆኖ ቀርቷል። እናም ይህ ለህወሃት 40ኛው የልደት በዓል ተብሎ እየተዘጋጀ ያለው በዓል የትግሉን ታሪክ ለመዘከርና ለማክበር ተብሎ ሳይሆን የስርአቱ ስልጣን ለማራዘም፤ ቅስቀሳዎች ለማካሄድና የድርጅቱ ተጠቃሚዎችና አጃቢዎች እንዲዝናኑበት ተብሎ እየተዘጋጀ ያለው በዓል መሆኑን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል።