Wednesday, May 20, 2015

በመቐለ ከተማ ውስጥ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ ህወሃት/ኢህአዴግን ወክሎ እንዲወዳደርና ህዝቡ እንዲመርጠው በተካሄደው ቅስቀሳ ላይ ወጣቱ እንዳልተቀበለው ተገለጸ።



   የገዢው ስርዓት ካድሬዎች የከተማውን ነዋሪ ህብረተሰብ ስብሰባ በመጥራት የምረጡን ቅስቀሳ እያካሄዱ በነበሩበት ሰዓት ወጣቱ ትውልድ በብዛት በተገኘበት ስብሰባ ላይ እኛ በእናንተ አስተዳደራዊ ስርዓት በደል ስለደረሰብን ይህንን መራራ ህይወት የሚቀይር መንግስት ነው የሚያስፈልገን እናንተን የምንመርጥበት ምክንያት የለንም በማለት በግልፅ እንደተቃወማቸው ተገለፀ።
    ስርዓቱ እያጋጠመው ያለውን ተቃውሞ ለመሸፈን ሲል የከተማዋ አስተዳዳሪ በካድሬዎቹና በአባላቶቹ በኩል ህዝቡን ለማደናገር ሲል ግንቦት 2/2007 ዓ/ም  የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካያካሂድ ጥሪ ቢደረግለትም ህዝቡ ግን ጥሪያቸውን በዝምታ ስለመለሰላቸው ለዝምታው በራሳቸው ፕሮግራም እንደተቀየረ አስመስለው ለቀጣይ እናካሂደዋለን እንዳሉ መረጃው አስታወቀ።
    ይህ በእንዲህ እንዳለ የገዥው ኢህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት ካድሬዎች በከተማው የሚታየው የህዝብ ተቃውሞ በጣም ስላሰጋቸው እናቶችንና አባቶችን በመሰብሰብ ልጆቻችሁ ተታልለው ለሌሎች ፀረ ህዝብ ተቃዋሚዎች እንዳይመርጡ በቤታችሁ ምከሯቸው በሚከሰተው ችግር ተጠያቂዎች እናንተ ናችሁ ብለው ቢያስፈራሯቸውም ወላጆች በበኩላቸው ግን ንግግሩን በመንቀፍ እድሜያቸው የደረሱ ልጆቻችን የፈለጉትን መምረጥ ይችላሉ መብታቸው ነው ማለታቸውን የተገኘው መረጃ አክሎ አስረድቷል።