አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የኋላ ቀርነትና
ስር የሰደደ ድህነት ማላቀቅ የሚቻለው የህዝባችንን ሙሉ ጤንነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው።
ይህንን እውን ማድረግ የሚቻለውም በምኞት ሳይሆን
በትክክለኛ ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል፤ ለሁሉም ዜጎች በጤንነት የመኖር መብት የሚያረጋግጥና ይህን አምኖ የተቀበለ
መንግስት መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው።
ባገራችን ውስጥ አሁን በምናየው ሁኔታ ግን በጤና ጉዳይ ላይ ልክ እንደሌሎች
ሴክተሮች ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርአት መፍጠር እንዳልቻለና ካድሬዎቹ እንደሚገልፁት የጤና ተቋማትን በበቂ
ደረጃ ተማልቷል ብለው ቢናገሩም ይህን ለማድረግ ግን የሞራል ብቃት እንደሌላቸውና የተሳካ ሁኔታ ላይ እንደማይገኙ፤ የኢህአዴግ መንግስት
ገንብቻቸዋለሁ የሚላቸው ጤና ጣብያዎችና ሆስፒታሎች የህብረተሰቡን ፍላጎት ያልመለሱ፤ ሰፊ የሆነ የግብአት ችግር ያላቸውና ለይስሙላ
ብቻ ጤና ጣቢያ አለ የሚባልበት ሁኔታ ነው ያለው።
የህክምና መሳሪያዎች፤ መድሃኒት፤ በቂ የሆነ የመታከሚያ ክፍሎችና ብቃት
ያላቸው ሃኪሞች በሌሉበት ሁኔታ ህንፃዎቹ ስለ ተገነቡና በሆስፒታሎቹ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታካሚ ወረፋ እየጠበቀ
በመዋሉ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኗል ማለት አይደለም፣ ወደ ሆስፒታሉ ለመታከም የሚሄደው ዜጋ ከፍተኛ እንግልትና የአስተዳደር
በደል እየደረሰበት ነው።
ልማቱን ለማፋጠንና የዳበረ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው የህዝቡ ጤንነት
ሲጠበቅ ብቻ ነው። እንደ ኢህአዴግ አባባል የጤና ጉዳይ ያገራችን ህዝቦች የልማት ጉዳይና የፍትሃዊነትና የእኩል ተጠቃሚነት ጉዳይ
ነው ብሎ ቢናገርም ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት አገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን አገልግሎቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ለማዳረስ ቅድሚያ
መስጠት ሲገባው የተቀመጠው ፖሊሲና ስትራተጂ ተራ ፅሁፍ ሁኖ እንዲቀርና ዜጎች በቂ የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ተደርጓል።
የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት በአገራችን ውስጥ ያለው የጤና ችግር 80 በመቶ
የሚሆነው መከላከል ይቻላልና መከላከልን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ማውጣት ላገራችን ይበጃል ብሎ ግልፅ ፖሊስና አቅጣጫ አስቀምጦ ወደ
ተግባር እንደገባ ነጋ ጠባ ህዝቡን ይቀሰቀሳል።
ነገር ግን
ስርዓቱ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ማግስት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተለይ በደርግ ስርዓት ግዜ ከነበሩ የጤና ጣቢያና የሆስፒታሎች ቁጥር
በብዛት መጨመራቸው ትልቅ ስኬት እንደተመዘገበ አድርጎ ቢናገርም ተጨባጭ እውነታው ግን ህንፃዎች ብቻ መገንባታቸው እንጂ ለሆስፒታሎቹ
የሚመጥኑ የህክምና መሳርያዎችና ብቃት ያለው ሓኪም እጥረት በስፋት የሚታዩበትና በየአመቱ ከሚታየው የህዝብ ቁጥር መጨመር አንፃር
ተገንብተዋል ተብለው የሚነገርላቸው ሕክምናዎች በእጅጉ አናሳ መሆናቸው ግልፅ ነው።
ለማጠቃለል-
-
የኢህአዴግ ስርዓት ራሱን አገራችን ውስጥ ከነበሩት ስርዓቶች እያወዳደረ
የሚናገረው የጤና ልማት ጉዳይ የሚደነቅ አለመሆኑና እንደ መንግስት መስራት የሚገባውን ባለመስራቱ ምክንያት ህዝቡ በሕክምና እጦት
ምክንያት በተከታታይ ችግር ላይ መሆኑ፤
-
መንግስት ያቀደው የልማት ስትራቴጂ ጤንነቱን የጠበቀ ዜጋ በመፍጠር እንጂ
በበሽታዎች የተጠቃ ህብተረሰብ ይዞ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደማይችልና ህዝቡ በከፋ ድህነት ውስጥ ስለሚኖር ካለው ተጨባጭ
ችግር አንፃር በቂ የአመጋገብና ምቹ የሆነ የአኗኗር ሁኔታ ላይ ስለማይገኝ ጤነኛ ዜጋ መፍጠር አልተቻለም።
ስለዚህ ባገራችን ያለው የጤና ልማት ሁኔታ ስርዓቱ እንደሚለው ሳይሆን በጥራት
ደረጃው፤ ከባለሞያው ብቃት እስከ መድሃኒት አቅርቦቱና አጠቃላይ በውስጡ ያለው የአስተዳደር ስርዓት አስከፊ ደረጃ ባለበት ባሁኑ
ወቅት ስለዚሁ ተቋም እድገትና የልማት ሁኔታ በማንሳት የሚደረግ ክርክር ትርጉም ሊኖረው አይችልም።