Sunday, July 26, 2015

በቂ ጥናት ያልተደረገበት ያገራችን የግብር አከፋፈል ስርዓት!!



በአንድ አገር ውስጥ ግብርን መክፈል ግዴታ ቢሆንም በሃገራችን እየታየ ያለው የግብር አከፋፈል ስርዓት ግን በጭፍን የሚካሄድና ለአያሌ ዜጎቻችን ወደ ድህነት አዘቅት ያስገባ ሲሆን በተቃራኒው የኢህአዴግ ባለስልጣኖችን ኪስ ከአቅሙ በላይ እንዲወፍር የሚያደርግ አሰራር  እየተፈጸመ ነው።
    በዚህም ምክንያት ንሯችንን እንለውጠዋለን በማለት በንግድ ስራ ዘርፍ ሲሳተፉ የቆዩትን ዜጎች ጥናት በሌለው የኢህአዴግ ስርዓት የግብር አከፋፈል ምክንያት ትርፍ አግኝተው ንሯቸው ለመምራት ይቅርና የነበራቸውን ሃብት አራግፈው ድርጅታቸው በመዝጋት ከስራ ውጭ የሆኑ ነጋዴዎች እጅግ በርካታ ናቸው።
    ማንኛውም መንግስት ግብርና ቀረፅ ተገቢነቱ በጠበቀ አካሄድ ከህዝቡ ሲሰበስብ የአገሪቱን እድገት ማረጋገጥ ለማስቻልና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ለመገንባት፤ የሰራተኞች ደመወዝ ዕድገት እንዲያሳይና ሌሎች እድገቶች እንዲመዘገቡ ተብሎ ነው፣ ነገር ግን ያን ያህል ግብር እየተሰበሰበ አገራችን ውስጥ ያለው የመንግስት ሰራተኛ እንኳን ስንመለከተው። የእለት ኑሮውን ከእጅ ወደ አፍ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው።
    በአሁኑ ግዜ በሃገራችን ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ በህክምና እጥረት ምክንያት የሚሞት፤ የተደራጀ ትምህርት ቤት ባለመነሩ በዳስ ሆነው ለፀሃይና ለንፋስ እየተጋለጡ የሚውሉ ተማሪዎች ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፣ ይህ ሁሉ ያገራችንን ነጋዴዎች በማሳደድ ወደ ድህነት እያስገባ የሚሰበሰበውን ግብር የህዝቡን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደ መሪዎቹ ካዝና እየገባ የጥቂቶች ባለስልጣኖች መንደላቀቅያ ሲሆን እየታዘብን ነው።
    ይህ ዓይነት አካሄድ ከሃገሪቱ የግብር አዋጅ ውጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ነጋዴዎቹ ወደ ከፋ ኪሳራ የሚያጋልጥ መሆኑና የግብር ስርዓት አከፋፈሉም በሦስት ደረጃዎች እንዲከፈል በማድረግ በተለይ በሦስተኛ ደረጃ ያሉትን ወገኖች በግምት እንዲከፍሉ ስለሚደረግና ግብሩን የሚሰበስበው ባለስልጣን ህብረተሰቡ የማይገባውን ግብር እንዳይከፍል መሬት ላይ ወርዶ በቂ  ጥናት ስለማይደርግ ለተከሰተው ችግር ዋነኛው ምክንያት ሆነዋል።
    ሌላው ተጨማሪ ችግር ደግሞ ያለፈውን ዓመት በወቅቱ ተከታትለው ግብር እንዲከፈል ማድረግ እየተገባቸው ተመልሰው የተዘጋውን ሂሳብ እንደ አዲስ ስለ-ሚከፍቱት አሁኑ ወደ ሚከፍሉት ግብር ተጨምሮበት ተደራራቢ እዳ ስለሆነባቸውና ከፍተኛ የስነ አእምሮ ጫና በመፍጠር ፍፁም ወደ ሆነው ድህነት እንዲገቡ እየተደረገ ነው።
    ይህ በአገራችን እየተካሄደ ያለውን የግብር አፋፈል ሁኔታ ለባለ ድርጅቶችና ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ ለሆነው ማህበረሰብም ቢሆን በንግድ ድርጅቶች ውስጥ ገብቶ ለመግዛት በሚፈልግበት ሰዓት ከእቃው ትክክለኛ ዋጋ ተጨማሪ 15 ከመቶ የእሴት ታክስ ለመክፈል እየተገደደ መሆኑና ለአዳንድ ባለ ድርጅቶች ከህዝቡ የሚከፈለውን ተጨማሪ የእሴት ታክሱ ገቢ እንዲያደርጉት ሲደረግ ጉቦ ለሰጡ ነጋዴዎች ግን ከህጋዊ አሰራር ውጭ በሆነ መንገድ በጥቅም በመተሳሰር የተሰበሰበውን ገንዘብ በጥቂት ነጋዴዎችና ባለስልጣናት እጅ እንዲገባ እያደረጉት ነው ያሉት።
    ከአግባብ ውጭ በሆነ መንገድ ግብርና ታክስ እንድከፍል ተጠይቄያሎህ የሚለውን የህብረተሰቡ ብሶት እንድያዳምጡ ተብለው የተመረጡት ሰዎችም ቢሆኑ የስርዓቱ አገልጋይ በሆኑት በክልሉ አስተዳዳሪ፤ በከተማ ከንቲባዎች፤ በዞንና በወረዳ አስተዳዳሪዎች የሚመሩ ስለሆኑ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ቀውስ ከመፍጠሩ በላይ ግብር በዛብን ብለው ወደ ሚመለከታቸው ባለ-ስልጣናት ይግባኝ ብሚጠይቁበት ሰዓትም ከታዘዙት ግብር መጠን ግማሹን ቅድምያ እንዲከፍሉ ስለሚገደዱ ለበርካታ አመታት ላባቸውን አፍስሰው ካሰበሰቡት ገንዘብ ምንም አይነት ማንቀሳቀሻ ሳያስቀሩ ለመክፈል ስለሚገደዱ መፍትሄ ሳያገኙ እየተጉላሉና ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ ናቸው።