Tuesday, May 2, 2017

ሰብዓዊነት የሌለው የሰብዓዊ መብት ተጣባቂ አይሆንም



ህዝብንና አገርን ወክሎ መንበረ ስልጣንን የያዘ መንግስት ወይም ገዥ ፓርቲ በግንባር ቀደምነት ተግባራዊ ሊያደርገው የሚገባ ነገር ካለ የዜጎቹን ዋስትና ሊጠብቅበት የሚችል ህገ መንግስታዊ መብቶች በማረጋገጥ ለዘላቂ ሰላምና እድገት ሊቆም ይገባል። ምክንያቱም አገር ማለት ዋናው ህዝብ ነው። በአገሪቱ የሚኖር ዋስትናው የተረጋገጠለት ህዝብ ደግሞ በሁለተናዊ የአገር እድገትና ግንባታ ባለቤት ይሆናል ማለት ነው።
  ህዝብን ባለቤት ያደረገ መንግስት ደግሞ ለሚያፋጥናቸው ታላላቅም ይሁን ትናንሽ ስራዎች ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት ነው። የህዝብ ዋስትናንና ወሳኝነትን የማያከብር መንግስት ደግሞ ህዝብንና አገርን ወክሎ በስልጣን የሚቀጥልበት ቦታ የለውም።
  በስልጣን ሊያቆየው የሚችል መንገድ ካለ ደግሞ አንድ ብቻ ነው። እሱም በህገ መንግስቱ የሰፈሩ የዜጎችን መብት እየናደ በወገኖቹ ላይ በሃይል ጨፍልቆ የህዝብንና የአገርን ሃብት በጥቂት ግለኞች እየተቀማ የተለያዩ ምክንያቶችን እየሰጠበት ለመኖር መጣር ብቻ ነው። ስለዚህ በዚህ መንገድ ሞክረው በብዙሃኑ ክንድ የወደሙ መንግስታት ወደ ሌሎች አገሮች ሳንሄድ በአገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማየት በቂ ነው።
  በዚህ መሰረት ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ ከጨቋኝ ወደ ጨቋኝ እየተሸጋገረች ዜጎች ዋስትናቸውን የሚያረጋግጠው ህገ መንግስታዊ መብታቸው እየተጣሰ ነፃነታቸውን አጥተው በጎስቋላ ኑሮ፤ ድህነትና እንግልት እያለፉ በትግላቸው አምባገነኖችን እያስወገዱ እንደመጡ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው።
   ዛሬም ለዚህች አገር በኃይልና በማደናገር ስራዎች መንበረ ስልጣን ይዞ ሲጓዝ የቆየና ያለው ገዥ ስርዓት ኢህአዴግና ተለጣፊ አጋር ድርጅቶቹ ስናይ ደግሞ የህዝብን ውክልናና ፍላጎት አግኝቶ ሊቀጥል ቦታ የለውም።
   ታዲያ ስለምን በስልጣን ይቀጥላል ከተባለ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚሰራቸው ስህተቶቹና አረመኔያዊ ተግባሮቹ ከህዝብ እንደሚነጥለው በሚገባ ስለሚያውቅ፣ ህዝብን ለመጨፍጨፍ ባሰማራቸው የፀጥታና የስለላ  ኃይሎች አድርጎ አፍኖ ለመያዝ የሚጠቀምበት ጊዜያዊ ከለላ ለማድረግ በህገ መንግስቱ ላይ ያሰፈራቸውን ስማዊ የዴሞክራሲ አቋሞች በማፈን የዜጎችን ነፃነት በመንሳት ወደወጣለት ጨቋኝነትና አምባገነናዊ አስተዳደር በመጠናከር እንዲሁም በህዝቦች መካከል ውስጥ ለውስጥ ባቀጣጠለው የማይቀዘቅዝ እሳት እርስ በርሳቸው እንዲጠራጠሩና አንድነታቸው እንዲሻክር አድርጎ ወደ ሌሎች ሃይሎች በመለጠፍ እያደናገረ በስልጣን ለመቀጠል አማራጭ የሌለው  መንገዱን አጠናክሮ እየሰራበት ስላለ ነው።
  ስለሆነ ደግሞ ህዝባችን በዚህ ስርዓት በላዩ ላይ በሚደርስበት በደልና አፈና ህገ መንግስታዊ መብቱን መሰረት አድርጎ ላነሳው የዴሞክራሲ፤ የልማት፤ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ በጠመንጃ ሃይል ለመጨፍጨፍ ተፈርዶበታል። ይህ በመሆኑ ደግሞ ተገዶ ቁጣውን ለመግለፅ ወደ አደባባይ በመውጣት ወደ አመፅ ሊያመራ ችሏል።በዚህ ድርጊት የጠፋ የኑጹሃን ወገኖች ህይወት፤የደረሰ የአካል ጉዳት የወደመ  ሃብትና ንብረት በነፃና ገለልተኛ አካል ቢፈተሽ ሃቁ ገሃድ በሆነ ነበር።
  የጨቋኙ የኢህአዴግ ቡድን የዚህ ሁሉ ጠንቅ መንስኤና ፈፃሚ ሆኖ እያለ እራሱ በወከለው የሰብዓዊነት ስሜት የሌለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዚህ ሰሞን ስርዓቱ ከሰኔ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም በንፁሃን ወገኖች ላይ የተፈፀመ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አጠናሁ ብሎ፣ ለዚህ የህዝብ ውክልና ለተነፈገው ፓርላማ ያቀረበው ሪፖርት በሚመለከት የሽንፈቱ ማሳያና የዚህ ሰይጣናዊና እከይ ቡድን ጥገኛ መሆኑን በግልፅ አሰምቷል።
 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሁን አጣሪ  ኮሚቴ አሰማርቸ  በኦሮሚያ፤ በአማራና በደቡብ ክልሎች መሰረት አድርጌ አጥናሁ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሚመለከት ያወጣው ሪፖርት እውነታውን ለባለቤቱ ለብዙሃኑ ህዝብ እንተወውና፣
  በመሰረቱ ይህ ቡድን ዴሞክራሲያዊ መብትን ለማግኘት ለጠየቀና ህገ መንግስታዊ አቋሞችን መሰረት አድርጎ ወደ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ለገለፀ ህዝብ በኢህአዴ የፀጥታ ሃይሎች የተኩስ እሩምታ ንፁሃን ዜጎች ሲያልፉ፤ በዱላ እየተቀጠቀጡ አካላቸው ሲጎድልና አስለቃሽ ጋዝ እየተወረወረባቸው ተደራራቢ ከባድና ቀላል ጉዳት እየደረሰባቸው ንፁሃን ወገኖች በጥርጣሬ አይን እየታዩ ወደ እስር ቤቶች እየገቡ ባልፈፀሙት ወንጀል እመኑ እየተባሉ ሲሰቃዩ የቆዩና ያሉ እንዲሁም በስውር ታፍነው አድራሻቸው ለጠፉ ዜጎች ለመዋስ  የሰብዓዊነቱ ማሳያ የከፈለው መስዋዕትና አስተዋፅኦ ምን አለ ከተባለ የለም ነው መልሱ።
ስለዚህ ንፁሃን ዜጎች በአውራ መንገዶች ህይወታቸውን እያጡ ህገ መንግስታዊ መብታቸው እየተጣሰ አንገቱን ደፍቶ የሚያይና የሚታዘብ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚደርሰው ጉዳት የሚያካሂደው ማጣራት ሰብዓዊነትን አያረጋግጥም።
  ምክንያቱም ለዜጎች መብትና ዋስትና የሚቆምና የሚከላከል ኮሚቴ ወይም ኮሚሽን፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ተጣባቂ በህገ መንግስት የተፈቀደላቸው ሁሉም መብቶች ሳይሸራረፉ በተግባር ለማዋል የሚከራከርና ሲጣሱ ደግሞ ወንጀለኛውን በወቅቱ ተከታትሎ ወደ ህግ ፊት በማቅረብ የዜጎችን መብትና ደህንነት ሲዋስ ነው። ካልሆነ የወንጀለኛው አካል ጥገኛ ሆኖ የሚካሄድ የሰብአዊ መብት ማጣራት ሰብዓዊነትን አያረጋግጥም።

No comments:

Post a Comment