Thursday, June 15, 2017

የኢህአዴግ መጥፎ ፖሊሲና አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ



     የአገራችን ርዕሰ ከተማ እና የአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ በውጭ ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ሕንፃዎችንና ተቋሞችን በዓይን አሻግሮ ለተመለከተ አካል የእድገትና የብልፅግና እምብርት ሆናለች ብሎ ከስርዓቱ ፕሮፖጋንዳ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ሊገልፅ ይችል ይሆናል።
    ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ በእድገትና ብልፅግና መንገድ ላይ ሳትሆን የኢህአዴግ የጥፋት ፖሊሲና ውድቀት መፈተኛ ማዕከል፤የባለፀጋዎችና የስርዓቱ ባለስልጣናት መኖሪያ እየሆነች፥ድሃዎችን እያፈናቀለች ለተለያዩ ማህበራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ውድቀቶች እያደረሰችባቸው ይኖራሉ።
    በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ ህዝብ ውጤት በሌላቸው በየጊዜው የሚገላበጡ አዋጆችና መምሪያዎች ተጋላጭ እየሆነ እንዲሰቃይ ያደርጉታል። የዚህ ክስተት በቅድሚያ ተነስቶ ሊታይ የሚችለው አገሪቱን ወክሎ እየገዛ ያለው ገዥው የወያኔ ኢህአዴግ ፓርቲ በተከታታይ የሚያገላብጠው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አንዴ ፊንፊኔ ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባት ልዩ ጥቅም እየተባለ እየታመሰ ያለውን አካሄድ መጥቀስ ይቻላል።
     የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ብልሹ አስተዳደር ስልጣን ላይ ከሚቆናጠጥ አንስቶ እስካሁን ለአዲስ አበባ ከተማ ችግር ግልፅና ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ሊያገኝ፤ መኖሪያ በሌላቸው ድሃዎች ላይ የሚደርሰው በደል ሊያበቃ፤ ከገዜ ወደ ጊዜ ድሃውን በመንጠቅ መሬት በጥቂቶች ሐብታሞች እጅ እንዲጠቀለል የማድረግ አካሄድ የጎላ ጥፋት መሆኑንና ከዚህም እንዲቆጠብ በየጊዜው ከከተማዋ ነዋሪ ህዝብ በተደጋጋሚ አቤቱታም ይሁን ጥያቄ ይደርስበታል።  
    ሆኖም ግን መንግስት በዚህ ተግባር ራሱ በቀዳሚነት ሲያደፈርስና ቅጥ ያጣ አሰራር ሲከተል በዚህ ልክ ደግሞ በአገሪቱ ሚዛኑን የሳተ የሃብት የበላይነትና የበታችነት ሊፈጠር ችሏል። ይህ የወለደው ደግሞ ድሆች በከተማዎች የመኖር እድላቸው እየጠበበና እጃቸውን አጣምረው የሚመለከቱበት ሁኔታ አስከትሏል። የዚህ ማሳያ ከ100 በላይ የሚሆኑ ወገኖችን በአንድ ቀን የበላውን የቆሼ አደጋ ማንሳት ይቻላል። የእለታዊ ፍጆታ እቃዎች ዋጋም ይሁን ሌሎች ነገሮች ግዣቸው እያሻቀበ ለዚህ የዕለታዊ ጉርስ የምትሆን የሌለው ዜጋ በከተማ የመኖር አማራጭ እየከበደው መጥቷል። ሐብታሞች ገንዘባቸውን በማንቀሳቀስ በሚያሰሯቸው ቤቶች በውድ እያከራዩ ለድሃው ያስቸግራሉ።
    ይህ ሁኔታ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዜጎች መካከል እየተፈጠረ ያለው ርቀቱ የተራዘመ የሃብት ከፍና ዝቅ እየተመለከተ ማረሚያና ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ሊያፈላልግ አልቻለም። በዚህም የተነሳ በርካታ ድሆች ለስደትና እንግልት ለመጋለጥ ይገደዳሉ። የድሃ ልጆች የሆኑ ከትምህርት ማድ አቋርጠው ወደማያስፈልጉ ተግባሮች እየተሰማሩ ለጎዳናዎች ሲጋለጡ ይታያሉ።
    በዚህ ልክ ደግሞ አገር ተረካቢ የሆነ ወጣቱ ትውልድ በሚገባ ተግንብቶና ተኮትኩቶ ማደግ እየተገባው ተስፋው እየጨለመ ትምህርት ሳይቀስምና ሳይገነባ በጅምሩ እየተበላሸ ራዕይ የሌለውና ለእለት ጉርሱ ብቻ የሚጠባበቅ ትውልድ እየሆነ እንዲሄድ ይገደዳል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የተማረ የሚባለው አካል ክፍል ቆጥሮ የሚያቋርጥና በዲግሪም ይሁን በዲፕሎማ ተመርቆ ስራ አጥቶ ከልተማረው ጋር እኩል በየመንገዱ ስራ አጥቶ ሲንከራተት ምንያህል ውስጣዊ ስሜቱ እየተነካ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ እንደሚፈጥር ለመገመቱ የሚያስቸግር አይደለም። 
    ስለዚህ አዲስ አበባ የባለሃብቶችና የወያኔ ኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደፍላጎታቸው የሚገላበጡባት ከተማ እንደሆነችና ነዋሪዎቿ የሆኑት ድኾች ደግሞ አሻግረው የሚመለከቷት በተለያዩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እየተሰቃዩ ነጋ ጠባ ፍትህ እያጡ ይገኛሉ። ከዚህ ባለፈም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፌደራሉ ትዕዛዝ እየተቀበለ የሚያካሂዳቸው የተለያዩ መድረኮች በማካሄድ በቴሌቪዥን መስኮት የህዝብን ምሬት እንታዘብ እንሰማ ይሆናል። 
    ሆኖም ግን የኢህአዴግ መጥፎ ፖሊሲ በተ ሙከራ ከመሆን ባለፈ የህዝቡን ችግር ፈትሾ ወደ መሬት ወርዶ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ሊያደርግ የሚችል አካል አልተገኘም። ይህንን ስንል ደግሞ ያላንዳች ምክንያት አይደለም። ካለፉት በቅርብ ጊዜያት ከተካሄዱት መድረኮች ብቻ በምናይበት ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብንና የመንግስትን ሃብት ከሚያጠፋፉትና የመልካም አስተዳደር እጦት፤ የፍትህ እጦት ወዘተ የሚታዩበት አስተዳደር እየተባለ ሲገለፅና በዚሁ ልክ ደግሞ ህዝቡ በተካሄዱት መድረኮች በግልፅ ችግሩን አውጥቶ ሲናገርና ሲነቅፍ ታይቷል።
    መከራውንና ችግሩን ተረድቶ ሊፈውስ የሚችል አካል ግን ሊያገኝ አልቻለም። የመልካም አስተዳደር መድረኮች ሂደት ዋጋ ቢስ ሆኖ ከቀረ በኋላ ደግሞ ዳግም ስሙን የቀየረው በጥልቀት የመታደስ ሂደት በሚል የወያኔ ኢህአዴግ ፈጠራ እስካሁን ውጤት ለሌላቸው መድረኮች ተካሂዶ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ወጥቶ ለመተግበር በመረባረብ ላይ እንዳለች በቴሌቪዥን መስኮት ሲገልፁ ታይተዋል።
     ምናልባት አንድ ጊዜ ወይም ሁለቴ ህዝብን ሰብስቦ ወዲያው ላልታዩት ችግሮች ባለቤት ለሆነው ህዝብ መድረክ ከፍተው ያለውን ችግር ለማወቅና ያበጠውን ቁስል ለማፈንዳት ህዝብ በወረንጦ እንዲነቅስለት እድል መስጠት መልካም ተግባር ቢሆንም ድክመቶቹን እንዳያርም ለቆረጠና የህዝብን ስልጣን በጠበንጃ ሃይል ጨፍልቆ ለቆመ ቡድን ግን መልካም ሳይሆን መጥፎ ተግባር ነው።
    በመሰረቱ እነዚህ ከህዳር 2008 ዓ.ም ጀምረው እስካሁን የተካሄዱትና እየተካሄዱ ያሉት የመልካም አስተዳደር መድረኮች ይሁን በጥልቀት መታደስ የሚባሉት ምን ውጤት አምጥተዋል? ሁሉም ሊጠይቀው ይገባል? አሁንስ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ያስፈለገበት ምክንያት ለምንድን ነው ሊባሉ ይገባል? ከዚህ ባለፈ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወያኔ ኢህአዴግ የመጥፎ ፖሊሲ ቤተ ሙከራ ከመሆን ባለፈ ህዝቦችን የሚቀይር ወይም ሊያሻሽል የሚችል ፍሬ ያለው ተግባር ከኢህአዴግ አንጠብቅም ሊባሉ ይገባል።

No comments:

Post a Comment