በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን ብዙ የአለማችን ሃገራት
ለዜጎቻቸው ኢኮኖሚያዊ ፤ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ማፋጠን እንደየምርጫቸው አሃዳዊ ወይም ፌደራላዊ የአስተዳደር ስርዓትን ይከተላሉ።
አገራችን ኢትዮጵያም የፌደራል አስተዳደራዊ ዘየን ከሚከተሉ ሃገሮች መካከል አንዷ ነች።የፌደራል ስርዓት ባህርያት ደግሞ የስልጣን
ክፍፍል፤የማንነት መከበርና ዴሞክራሲያዊነት ከብዙዎቹ ዋነኞቹ ናቸው።
ነገር ግን አገራችንን ለ26 ዓመታት በፌደራልዊ አስተዳደር ስርዓት እየመራሁ
ነው የሚለው ወያኔ ኢህአዴግ፣ አገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ ሲከታት እንጂ አንዱንም የፌደራል አስተዳደር መገለጫ ሲተገብር
አልታየም። ምክንያቱም ለዴሞክራሲ ግንባታ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያለው አመራር ከሌለ ፌደራላዊ መሆን ለብቻው ፋይዳ አይኖረውምና።
ወያኔ ኢህአዴግ ከመጀመሪያ ይህንን የአስተዳደር ዘየ በኢትዮጵያ ህዝብ
ላይ ሲጭን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተጠንቶ ሳይሆን ለስልጣን እድሜው ማራዘሚያ ይሆነኛል ብሎ እንጂ የህዝብ ይሁንታን አግኝቶ አይደለም።
በአሁኑ ጊዜ ይህ የሰይጣን ህገ መንግስት በፈጠረው ትልቅ ክፍተት ምክንያት፣
ለዘመናት በጋራ ተከባብረውና ተቻችለው ይኖሩ የነበሩትን የአገራችን ህዝቦች በቋንቋ፤ በዘር፤በሃይማኖትና በማህበራዊ አመጣጥ ልዩነት
በማድረግና በመከፋፈል ዛሬ ላይ አስከፊ ወደ ሆነ የእርስ በርስ ግጭት እየመራቸው ይገኛል። አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ
በነፃነት የመንቀሳቀስና በፈለገው ቦታ የመኖር መብቱን ተነጥቆ፥ የአካል ደህንነት፤ የነፃነት፤በህይወት የመኖር ሰብዓዊ መብቱን ተገፎ
በገዛ አገሩ ላይ እንደ አራዊት ይታረዳል።
ወያኔ እየተከተለው ያለው ትውልድ ከፋፋይ እስትራቴጅ አካባቢያዊ ማንነት
ነግሶ ብሔራዊ ወይም ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲደበዝዝ በማድረግ የኢትዮጵያን ህዝቦች የአንድነት ባህል በማዳከም በውስጣቸው መቃቃር
እንዲፈጠር አድርጓል።አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች የምንመለክተው የዜጎች መፈናቀልና ግጭት የዚህ ወያኔያዊ የጥፋት ሴራ ውጤት ነው።
ኢ-ፍትሃዊ በሆነና በእኩልነት ላይ ያልተመሰረተ አስተዳደርን በመከተል ለአንደኛው የማንነት እውቅናን ሰጥቶ ሌላውን በሃይል ጨፍልቆ
በመያዝ ማንነቱን እንዲያጣ ስለሚያደርግ ነው።
ዛሬ ላይ ወያኔ በፈጠረው የእርስ በርስ ጥላቻ የተነሳ ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት
ተቋማት መሆናቸው ቀርቶ የዘረኝነት ማራመጃ ቦታዎች እየሆኑ መጥተዋል። የኦሮሞ ተማሪዎች ጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ፤የትግራይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤
የአማራ ተማሪዎች ደግሞ በትግራይ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ለመማር እየተቸገሩ ያሉበትን ሁኔታ እየተመለከትን እንገኛለን። ወያኔ የሚፈልገው
ደግሞ እንደዚህ አይነቱን መከፋፈላችንን እንጂ አብሮነታችንን ስላልሆነ ሁኔታውን ለማስታገስ ከቸለልተኝነትና ሚዲያላይ ከማሻጠር በዘለለ
ሲሰራበት አይታይም።
የፌደራል ስርዓት ሌለኛው መገለጫ የሆነውን የኃይል ክፍፍል ስናይ ደግሞ
ፍትሃዊ የሆነ የስልጣን ክፍፍል የለም።ቁልፍ የጦሩ መሪዎችና የደህንነት ተቋማት በአንድ ኃይል ብቻ የተያዙ ናቸው። በስመ ኢህአዴግ
ተጠፍጥፈው የተሰረት ክልላችንን እንወክላለን የሚሉት ድርጅቶች ቅጥረኞች እንጅ የየክልላቸውን ስልጣን የሚወክሉም አይደሉም። በዚህም
የተነሳ የህዝብ አመኔታን በማጣት አሁን እየተመለከትነው ላለነው ህዝባዊ ዓመፆች እንዲቀጣጠል መንስኤ ሆነዋል።
የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና ዜጎች በቀጥታ በአገራቸው
ፖለቲካ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ የፌደራል ስርዓት የሚጨነቅላቸው መርሆች ሆነው እያለ፣ የወያኔው ፌደራሊዝም ግን
"ለሰይጣን አትስጠው ስልጣን" እንደተባለው በአገሪቱ ላይ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ከመስራት
ይልቅ፣ ስልጣኑን ለሃይል እርምጃ በመጠቀም አምባገነንነቱን የበለጠ አጠናክሮ እየቀጠለበት ይገኛል።አሁን ከወቅቱ ቁልፍ የመልካም
አስተዳደር እና የመሠረታዊ የስርዓት ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ዜጎች ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ህዝባዊ ትዕይንት በማድረጋቸው
ብቻ ለእስራትና ግድያ በመዳረግ ወደ ለየለት ፀረ ህዝባዊነት አስተዳደር ውስጥ በመግባት ስርዓቱ በንፁሃን ዜጎች ደም ተጨማልቆ ይገኛል።
በአጠቃላይ የወያኔ ኢህአዴግ እየተከተለው ያለው የፌደራል ስርዓት ትክክለኛውን
ፌደራላዊ ስርዓት ሳይሆን ለራሱ የስልጣን መቆያነት ከቀመራቸው ዘዴዎች ውስጥ ህዝቡን የአንድነት እሴቶቹን በማዳከምና በመከፋፈል
እርስ በርሱ እንዲበላላ ብሎም እንዲናጋ በማድረግ፥ በብሄሮች መካከል ገላጋይ መስሎ በመግባት የጥላቻ ቤንዚን እያርከፈከፈ በኢህአዴግ
ላይ የሚነሳውን ተቃውሞ አቅጣጫውን መቀልበስና እያደናገረ በስልጣን ላይ የሚቆይበትን መንገድ ማራዘም ነው።
ለዚህ ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ለፈጠረው የጥላቻ ግንብና የብሔሮች
ተቃርኖ "ለሰው ጠላቱ ይወጣል ከቤቱ" እንደተባለው አጠናክሮ እየሰራበት ይገኛል። ውጤቱ ደግሞ አሁን በአገሪቱ ላይ
ተከስቶ ያለው የፖለቲካ ቀውስ ነው። ይህ ደግሞ አገሪቱን ወደከፋ አቅጣጫ እየወሰዳት እንደሚገኝ ለማንኛውም አካል ትንታኔ የሚያስፈልገው
ጉዳይ አይደለም።
ስለዚህ ከአገር
በቀሉ ፋሽስት ወያኔ ኢህአዴግ ሰይጣናዊ ተግባር አገራችንንና ህዝባችንን ለማዳንና ሀገራችን አንድነቷን ጠብቃ ዜጎች
የኢትዮጵያዊነት እሴቶቻቸውን አጠናክረው በእኩልነት፣ በነፃነት፣ በሰላም እና በፍቅር እንዲኖሩ ለማድረግ፣ ወያኔ የለኮሰውን
የተቃርኖ ሰደድ እሳት ሁላችንም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከብረት በጠነከረ የአንድነት ክንዳችን ሣይቃጠል፤በቅጠል ልናጠፋው ይገባል።
No comments:
Post a Comment