Friday, March 16, 2018

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ወራት ያለምንም በቂ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል ያላቸውን በርካታ የንግድ ተቋማት ቢያሽግም፣ በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ግሽበት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡



  የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ እንዲደረግ ያዘጋጀውና በካቢኔ የፀደቀው የመካከለኛ ጊዜ የወጪ ማዕቀፍ ዕቅድ፣ በ2010 ዓ.ም. የዋጋ ግሽበቱ በነጠላ አኃዝ (ስምንት በመቶ) እንደሚሆን ተንብዮ ነበር፡፡ ነገር ግን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው የየካቲት ወር የዋጋ ግሽበት 15.6 በመቶ መሆኑን በመመልከቱ፣ የአዲስ አበባ የዋጋ ግሽበት ተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
  በተጠናቀቀው የካቲት ወር በርበሬ በኪሎ እስከ 150 ብር፣ ጤፍ እስከ 33 ብር፣ የሽሮ እህል እስከ 40 ብር፣ ዘይት በሊትር (የኑግ) እስከ 80 ብር፣ ድፍን ምስር እስከ 40 ብር ድረስ ለግብይት ሲቀርቡ የስኳርና የስንዴ ዱቄት በገበያ ውስጥ እጥረት እንደተፈጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡
 ኤጀንሲው ባወጣው መረጃ የየካቲት ወር የዋጋ ግሽበት በጥር ወር ከነበረው የ2.5 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በተለይ በጥራጥሬ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በርበሬና በቅመማ ቅመም ምርቶች ባልተለመደ ሁኔታ በተጠናቀቀው ወር የ50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ ተገልጿል፡፡
  ከዚህ በተጨማሪ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ አልባሳትና መጫሚያዎች፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች፣ የሆቴል ምግቦች፣ የጤና ወጪዎች በዋጋ ንረው መገኘታቸው ተመልክቷል፡፡

No comments:

Post a Comment