Friday, March 16, 2018

በኢትዮጵያ የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር አሻቅቦ 7 ነጥብ 8 ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን የዕለት ጉርስ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ፡፡



  ከባለፈው ዓመት የተረጂዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ ብልጫ እንዳለውና በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ 7 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች የሰው እጅ ጠባቂ ሆነው እንደሚዘልቁ ተነግሯል፡፡ በመንግስት እና በለጋሽ ድርጅቶች አማካይነት በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ከጥር 2010 እስከ መጪው ታህሳስ 2011 ድረስ ለ7 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰዎች የምግብ እርዳታ ለማቅረብ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገልጻል፡፡
  በችግር እና በድርቅ ውስጥ ለሚገኙት በሚሊየን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የአንድ ዓመት ቀለብ ለመሸመት 1 ነጥብ 4 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ከለጋሽ ተቋማት ጋር በጋራ በተሰጠው መግለጫ ተነግሯል፡፡ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ በመግለጫው ወቅት እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ እየተከሰተ ይገኛል፡፡
  ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ድርቅ ይከሰት የነበረው ቢያንስ በአስር አልያም በአምስት ዓመታት ልዩነት እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ተደጋጋሚ ድርቅ ተከስቶ በርካታ ዜጎችን እያጠቃ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ላለው ድርቅ የአገዛዙ የኢኮኖሚ እና ግብርና ፖሊሲ የራሱ አስተዋጽዖ እንዳለው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

No comments:

Post a Comment