Sunday, October 27, 2013

የሸራሮ ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገድ በኮብል ስቶን ንጣፍ እንዲሰራ የተያዘውን እቅድ በዲግሪና በዲፕሎማ የተመረቁ ተማሪዎች እንዲሰሩት ቢወሰንም በተግባር ግን ለሌሎች እየተሰጠ ነው፣




በወረደው መመሪያ መሰረት በድግሪና በዲፕሎማ የተመረቁ 245 ተማሪዎች በከተማዋ የሚሰሩ የኮብል ስቶን ንጣፍ ስራን በኮንትራት እንዲወስዱት የተወሰነ ቢሆንም በተግባር ግን ሌሎች የማይመለከታቸው 70 ሰዎች ግልጽነት በሌለው አሰራር እንዲጨመሩ በመደረጉ በተማሪዎቹና በአመራሩ ላይ አለመግባባት ተፈጥራል፣
ተማሪዎቹ ስራውን ለመምራት የተመደቡ ባለስልጣናት እየተከተሉት ያለ ቅንነትን የጎደለው አሰራር በወረደው መመሪያ መሰረት እንዲስተካከል ለሸራሮ ከተማ አስተዳዳሪ ክስ ለማቅረብ በሄደበት ጊዜ በፖሊስና ሚሊሽያ እንዲከበቡ በመደረጉ ረብሻ ተቀስቅሳል፣ በሁኔታው ስጋት የገባው የከተማዋ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገ/ማሪያም የጠየቃችሁትን ጥያቄ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ምላሽ እንዲሰጣችሁ ይደረጋል በማለት ተማሪዎችን ካረጋጋ ብሁዋላ ሦስት ተማሪዎችን የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ረብሻ ፈጥረዋል ተብለው በእስር ላይ እንደሚገኙ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፣
በሁኔታው የተቆጡት ተማሪዎች ጥቅምት 12,2006 ዓ/ም በቀሰቀሱት ተቃውሞ የከተማዋን አፈ ጉባኤ ደሳለይና የከተማ ልማት ሃላፊ አቶ ምዕባለን የደበደቧቸው ሲሆን ችግሩን ለመፍታት በታሕታይ አድያቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ወዲ አወጣሽ የሚመራ ስብሰባ ጥቅምት 14,2006 ዓ/ም መጀመሩን የደረሰን ዘገባ ጨምሮ ያስረዳል፣
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሽረ-እንዳስላሰ ከተማ ለሚሰራ የኮብል ስቶን ንጣፍ እያንዳንዱ ኗሪ ብር 500 እንዲያዋጣ መክፈል ያልቻለ ደግሞ ለ 10 ቀናት በጉልበት ስራ እንዲሳተፍ ለአምስቱ ቀበሌዎች በመመሪያ ምልክ የወረደ ቢሆንም ኗሪው እንዳልተቀበለው ቷውቋል፣