Monday, April 7, 2014

በአማራ ክልል የሚገኙ የአንድነት ፓርቲ አባላት ህዝብን ወደ ሽብርተኝነት ገፋፍታችኋል በሚል ምክንያት በገዥው መንግስት እየታሰሩና እየተሰቃዩ መሆናቸውን ተገለፀ።



በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ የአንድነት ፓርቲ አባላት በህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የኑሮ ችግር አስመልክተው በመናገራቸው ብቻ ህዝብን ከመንግስት ተቃራኒ እንዲሄድ ታደርጋላችሁ ይህ ደግሞ የአሸባሪዎች ስራ ነው በማለት የገዥው ስርዓት ባለስልጣናት ወደ እስር እየዳረጓቸው መሆኑን ከስፍራው የደረሰን  መረጃ አመለከተ።
     በመረጃው መሰረት በሰሜን ጎንደር ዞን ታስረው ከሚሰቃዩት ዘጠኝ የድርጅቱ አባሎች መካከል አቶ ተገኘ ሲሳይ፥ አቶ አምደማርያም ይሁን፤ አቶ ቢረሳው፥ አቶ ማሩ አሻግሬና ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሱ ሲሆኑ እነዚህ ወገኖች መጀመሪያ ጎንደር ከተማ በሚገኘው አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ከቆዩ በኋላ አሁን ግን የት እንደተወሰዱና አድራሻቸውን እንደማያውቁ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።    
     በተመሳሳይ በባህርዳር ከተማ 16 የሚሆኑ የአንድነት ፓርቲ አባላት በእስር ቤት ታጉረው እየተገረፉ ሲሆን ሲጮሁ ድምፃቸው እንዳይሰማና ምሬታቸውን እንዳይናገሩ አፋቸውን በፕላስተር ተሸፍነው እየተሰቃዩ መሆናቸውና ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘ አረመኔያዊ ተግባር በንፁሃን ወገኖች ላይ እየተፈፀመ ያለውን አሳዛኝ ፍፃሜ። የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ድምጽ መቃወም እንዳለበት አንዳንድ ወገኖች እየገለፁ መሆናቸውን መረጃው ጨምሮ አስታውቋል።