የአንድ ሀገር የእድገት መለኪያ የተረጋጋ
ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲኖርና የተለያዩ የልማት ግንባታዎች ተሰርተው የህዝቡን ጥቅም ሲያሟሉ፤ የእያንዳንዱ ዜጋ ገቢው ሲጨምርና የሀገሪቷ
እድገት በመሬት ተግባር ላይ ሲውል እንጂ በአፍ ብቻ የሚገነባ ኢኮኖሚና የእድገት ለውጥ የለም።
የኢህአዴግ ባለ-ስልጣናት የተወሰነ ኪሎሜትር
መንገድና ከበቂ በታች የሆኑ ሌሎች ግንባታዎች በመስራታቸው ብቻ በተለያዩ የመገናኛ ቡዙሃን ከሰሩት በላይ በዜናዎቻቸው ቃላት በመደርደር
በባዶ ሁኔታ ላይ ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት እንደአስመዘገቡ
አስመስለው ሲደሰኩሩ እየተሰሙ ነው።
እነዚህ ባለስልጣናት የእድገት ሽግግር እና
ትራንስፎርሜሽን እቅድ አዘጋጅተን የእርሻና ኢንዱሱትሪ እድገት እንዲፋጠንና በሌሎች ሴክተሮች ውስጥ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት፤ ስራ
አጥነት በማስወገድ የያንዳዱን ዜጋ ገቢ በመጨመር የድህነት ደረጃን ለመቀነስና ተረት ለማድረግ ያለመ እቅድ ነው እያሉ ሲለፈልፉ
ይታያሉ።
ስልጣንን በሞኖፖል ተቆጣጥረው ሃላፊነታቸው ከለላ በማድረግ ባህር ተሻግረው
ከመጡ ኢንቨስተሮችና ተቋማት ጋር በመተባበር የሀገር ሃብት አብረው እየመዘበሩ የሚገኙት እነኝህ ባለልጣናት ለመገመት በሚያስቸግርና
በሚገርም ሁኔታ ሚሊየነሮች መሆናቸው ላገራችን ህዝብ የተደበቀ ጉዳይ አይደለም።
የኢህአዴግ ስርአት ኢትዮጵያ ፈጣን በሆነ
የልማት መንገድ እየተራመደች ነው እያሉ ሲለፈልፉ አለማቀፍ የገንዘብ ተቋም I.M.F በበኩሉ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ኢህአዴግ
እንደሚለው በ11 ፐርሰንት ሳይሆን አስመዘገብነው የሚሉትን ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ከሃቅ የራቀ የኢኮኖሚ እድገት መለኪያ በድህነት
ብዛት ሆዱ ታጥፎ እያደረ ላለው የጭቁኑ ወገናችን ኑሮ ግምት ውስጥ ያላስገባ ባዶ ጩኸት ነው።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለው አለማዊ ሁኔታ ተዛምዶ ባለመሄዱ ምክንያትና የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ አገራችን
ውስጥ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ባለመስማማቱ ከ33 እስከ 46 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ቢደረግም ስርዓቱ የገበያውን ሚዛን ለመጠበቅ
ከብሄራዊ ባንክ 10.3 ቢልዮን ብር ወደ ገበያ እንደወረደ ቢገልፅም የማንኛውም አይነት እቃ ዋጋ አስደንጋጭ በሆነ መንገድ ሲጨምር
ታይቷል።
የወያኔ ኢህአዴግ ባለስልጣኖች ኢትዮጵያ በ2020 ዓ/ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው
አገሮች ተርታ ትሰለፋለች እያሉ ባሉበት ባሁኑ ጊዜ የአገሪቱ ብር ከልክ በላይ አሽቆልቁሎና የመግዛት አቅሙ በሚያስገርም ሁኔታ ወርዶ
ያለበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፣ ሸቀጣ ሸቀጦች በተለይ የእህል ዋጋና የመሳሰሉትን ነገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ገበያ ላይ ሲገኝ፤ የዋጋ
ንረት ሲረጋጋና የእያንዳንዱ ሰው ገቢ ሲጨምር እድገት ተመዝግቧል ብሎ ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል።
እየታየ ያለው ነገር ግን በተለይ እንደ
ስኳር፤ ዘይት የመሳሰሉት ነገሮች ከገበያ ጠፍተው ህዝቡ እለታዊ ኑሮውን ለመምራት መጠናዊ ፍላጎትን ለማሟላት የተቸገረበት ሁኔታ
ላይ ይገኛል፣ በዚህ ላይ መንግስት የራሱን ውድቀት ለመሸፋፈን ሲል በየከተማው ለሚገኙ ነገዴዎች ሆን ብላችሁ ገብያውን በማወክ ችግር
እየፈጠራችሁ ነው በማለት የንግድ ድርጅታቸዉን እንዲዘጉ በማድረግ ወዳልተፈለገ ችግር እንዲገቡና ሁኔታው ይበልጥ ተባብሶ እንዲቀጥል
እያደረገ ይገኛል።
ለማጠቃለል አገራችን ውስጥ ፈጣን እድገት እየተመዘገበ ነው ተብሎ እየተነገረለት ያለውን ባዶ ጩኸት ኢህአዴግና
እና የውጭ ሃይሎች በጋራ ሆነው የሀገራችን አንጡራ ሃብት ለመዝረፍ
እንዲመቻቸዉና የተስፋ ዳቦ እየቆረሱ ህዝቡን ለማደናገር እንጂ የአገሪቷን እድገትና የህዝባችን የኑሮ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መገመት
በሚስቸግር የድህነት አዘቅት ላይ መዘፈቋ እምብዛም የሚያድናግር አይደለም።