Tuesday, September 2, 2014

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በመተማ አካባቢና አብደራፊዕ ከተማ የሚገኙ በማህበራት ተቀጥረው የሚሰሩ ሴት እህቶቻችን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች እየተገደሉ መሆናቸውን ምንጮቻችን አስታወቁ።



  ምንጮቻችን እንዳስታወቁት በአብደራፊ ከተማ በማህበር ተደራጅተው በስራ ላይ ተሰማረትው ከሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች ተቀጥራ  ስትሰራ የነበረች አዲሳ የተባለች ዜጋ አካባቢው ሰለም ነው በማለት ብቻዋን ቀርታ ስትሰራ በነበረችበት ሰዓት ሰኔ 12 /2006 ዓ.ም ባልታወቁ ሰዎች ተገድላ እንደተገኘች ለማወቅ ትችሏል።
   በአካባቢው የሚገኙ ‘የስርዓቱ የፖሊስ አባላት ስትሰራበት በነበርችው ማህበር ለሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች የሞተችውን ዜጋ የገደላችኋት እናንተው ናችሁ ወይም የገደላትን ሰው ታውቁት አላችሁ በማለት አስረዋቸው እንደሚገኙ ምንጮቻችን አስታውቀዋል።
   ታስረው ከሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች ውስጥ የተውሰኑትን  ለመጥቀስ ነጋሲ ግርማ፤ ብርሃነ የተባለ የመኪና ሹፌር፤ ኪዳነ የተባለ ግለሰብ የሚገኙባቸው ዘጠኝ ሰዎች ታስረው እንደሚገኙ መረጃው አስታውቋል።
    በተመሳሳይ አብደራፊዕ ከተማ የሚገኙ ፖሊሶች ንፁሃን ዜጎችን በመግደልና በማሰቃየት ስራ ላየ ተጠምደው የሚገኙ ሲሆን በዚህም የተናደደው የአካባቢው ህብረተሰብ ለመበቀል ሲል በላያቸው ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተገልጿል።
   በምንጮቻችን መረጃ መሰረት ነሓሴ 20 /2006 ዓ/ም ይርጋ ተጫኔ የተባለ ሞላሌ እንደሻው ለተባለው ረዳት ኢንስፔክተር ከነእህቱ እንደገደለው በመግለፅ ለዚህ ተግባር እንዲፈፅም የተገደደበትን ምክንያንት ሲገልጽም ከዚህ በፊት ወንድሙን ገድሎ የመንግስት ካድሬ  በመሆኑ ብቻ በህግ ፊት ቀርቦ ስላልተጠየቀ የወሰደው እርምጃ እንደሆነ ገልጿል።
   ከከተማዋ ሳንወጣ ሃምሌ 27 /2006 ዓ.ም የከተማዋ ፖሊሶች ለሁለት ሰዎች ለየት ባለ መንገድ አስረው እያሰቃዩዋቸው ከቆዩ በኋላ ካህሳይ ተወለ ለተባለው ዜጋ ሲገድሉት ንጋቱ ወጋየሁ ለተባለው ደግሞ በግርፋት ብዛት አይምሮውን ስቶ ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደ ምንጮቻችን ጨምረው ከቦታው አስታውቋል።