Saturday, October 18, 2014

የፍዳ ቀጠሮ!!



የመጀመርያ ክፍል!
የተከበራችሁ ወድ ተከታታዮቻችን ለዛሬ የፍዳ ቀጠሮ በሚል ርእስ የተፃፈውን የመጀመርያ ክፍል እናቀርብላቹኃለን።
    ቀጠሮ በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል፣ ባንድ በኩል ደስታን የያዘ የምንጓጓለት ነገር። እልባት ወይም መፍትሄ አግኝቶ የምንደሰትበት ብስራት የምናበስርበት ወ.ዘ.ተ ሲሆን። ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ አንፃራዊ የሆነ ነው፣


ምሳሌ።- የዳኞች የብይን ቀጠሮ ባንድ በኩል ከተከሰስንበት ወንጀል ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ፍርድ የምታገኝበት ሲሆን። ከተወሰነብን እና ወደ ወህኒ ከተወረወርን በኋላ። ያለ የሌለ አንጡራ ሃብታችንን አቧጦ የሚውስድ ውሳኔ ከተወሰነብን ደግሞ ቀጠሮው የፍዳ ይሆናል፣
    ይሁን እንጂ ባገራችን ኢትዮጵያ ፍትህ መስመሩን ይዞ ስለማያውቅ ለጥቂት አለቅላቂዎች ካልሆነ በስተቀር ቀጠሮዎች ሁሉ። የመከራ፤ የእንግልትና የስቃይ እንጂ። ብስራትን ይዘው የሚመጡ እውነተኛ ፍትህን የተላበሱ፤ ፍትሃዊ አሰራርን የሚያንፀባርቁ ሲሆኑ ማየት። እንዳለመታደል ሆኖ እስካሁን አልተለመደም፣
    በአፄዎች ዘመነ-መንግስት ጀግኖች ወደ ዙፋን እንዲመጡ ተቀጥረው። በሰይፍ የሚቆረጡበትና በገመድ ታንቀው የሚንጠለጠሉበት ታሪክ አሳልፈናል፣ የነሱን ፈለግ ተከትለው የመጡ ስልጣናቸውን በጦር መሳርያ የጨበጡ አምባገነን መሪዎችም ስቃያችንን ከድጥ ወደ ማጡ በማድረግ ለመስማት የሚዘገንኑ፤ ለማየት የሚቀፉ፤ ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠሉ ኢ-ሰብአዊ የሆኑ አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈፅመው ያለፉት አለፉ። ያሉት ደግሞ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፣
    ላለፈ ክረምት ገሳ አይሰራም ነውና። ያለፈውን እዚያው ለታሪክ ትተን የወቅቱን “የፍዳ ቀጠሮ” ለመዳበስ ያህል ጥቂት እንበል። ለሁሉም እንደሰራው የሚወቅስና የሚያቆላምጥ ያው ታሪክ ነውና፣
    የወቅቱ በማጭበርበር የታጀበ “የፍዳ ቀጠሮ” የተጀመረው እንደ ራሳችን አቆጣጠር በ1987 ዓ/ም ነው፣ ስልጣን ከተያዘበት ማግስት ጀምሮ ያ ሁሉ ለህዝብ ታገልን፤ ነፃ እውጪዎች ነን እያሉ። ሲመፃደቁበት የነበረውን የፈሰሰው የሰማእታት ደምና የተከሰከሰው አጥንታቸው ይፈርደናል ሳይሉ  “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን ግን አላይ” አድረገውት አረፉ፣ በእርግጥ በወቅቱ ከግራም ከቀኝም ተሰብስቦ ራሱን አደራጅቶ የተንቀሳቀሰ ይህን ያህል ሃይል ስላልነበረ ስርአተ-ወያኔ-ኢህአዴግ ያን ያህል ሳይጋለጥ። ራሱን በማስመሰል ደብቆ “የቀበሮ ባሃታዊ” ሆኖ ቆይቷል፣ ይሁን እንጂ ውስጡ ለሚያውቁት ግን የአደባባይ ምስጢር ስለነበረ። ታሪክ ይቅር የማይለው ብዙ አሰቃቂ ድርጊት መፈፀሙ ስውር ሆኖ አልቀረም፣
    እያደረ እየዋለ ግን “እውነትና ምንጭ እያደረ ይጠራል” እንደሚባለው። በቀጣዮቹ ሁለት ቀጦሮዎች ማለትም በ1987 እና በ1997 ዓ/ም መካከል። ታጋሹ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ብዙ ደባዎችን ማየት ቻለ። ከዋና ዋናዎቹ መካከል ብዙዎች በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ከተወለዱበትና እትብታቸው ከተቀበረበት ውድ ሃገራቸው ተሰደዱ፤ ታሰሩ፤ እንዲሁም ህይወታቸውን አጡ፣
     የሃገራችን እንቁ የሆኑ ብርቅየ ምሁራን በአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ታድነው አድራሻቸው የውሃ ሽታ ሆኑ፣       “ታጋይ ይሞታል። ትግል ግን አይሞትምና” ሚሊዮኖችን  በማነሳሳት በትግል እሳት አቀጣጥሎ ከነዚህም አንዱ  ቅንጅት ላንድነትና ለዴሞክራስን ያህል ፓርቲ መፍጠር ችሎ ነበር፣ የወያኔን ማሌሊታዊ ሴራ ጠንቅቀው ያላውቁ ሃገር አፍቃሪዎች ወደ አዋጪው የአፈሙዝ ትግል እንደሚቀየር ያልተረዱትንና በማስመሰሉ የተደናገሩት ደግሞ። ስላማዊና ፖለቲካዊ ትግሉን አፋፍመው ተያያዙት፣