Tuesday, October 14, 2014

ከኢትዮጵያ ድህነት መጥፋት ያልቻለበት ዋናው ምክንያት ያለፉት ገዢ ስርአቶች ናቸው ሲሉ የወያኔ ኢህአዴግ አመራሮች ያቀረቡት ሃሳብ በህዝቡ ተቀባይነት እንዳለገኘ ተገለፀ፣




የመቐለ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ያገራችን አካባቢዎች በኢህአዴግ ካድሬዎች ስብሰባ መካሄዱን የገለፀው መረጃው፤ የስብሰባው አጀንዳም ባገሪቱ እየተካሄደ ያለው የልማት፤ የሰላምና የህዳሴ ጉዞ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ አገራችን ውስጥ የተንሰራፋው የድህነት ሁኔታ ያለፉት ገዢዎች ትተውልን የሄዱት ጠባሳ ነው፤ የኢህአዴግ ድርጅት ድህነቱን ለመቅረፍ ብዙ ቢንቀሳቀስም ነገር ግን ስር ሰዶ ስለቆየ ማጥፋት አልቻልንም። ስለዚህ ህዝቡ ይህንን ማወቅና መረዳት ይኖርበታል የሚሉና ሌሎች አርእስቶች አስነስተው ለመወያየት ቢሞክሩም፤ ስብሰባው ላይ የተገኘው ህዝብ ግን እንዳልተቀበላቸው ምንጮቻችን ያደረሱን መረጃ አስረድቷል፣
    መረጃው በማስከተል ምክትል ከንቲባና የልማት ክፍል ሃላፊ የሆነው አቶ ኣሰፋ ተገኘ የመቐለን ከተማ ህዝብ ሰብስቦ መንግስታችን ህዝቡ ከድህነት እንዲላቀቅ ከፈፀማቸው ተግባራት አርሶ አደሩ የራሱ የሆነ ቋሚ ሀብት እንዲኖረው፤ የመሬት ባለቤትነት እንዲረጋገጥለት ተደርጓል ሲል ላቀረበው ሃሳብ፤ ስብሰባው ላይ የተገኘው ህዝብ እንደተቃወመውና፥ በህዝቡ የቀረበውን የተቃውሞ ሃሳብም አርሳደሩ የመሬት ዋስትና አግኝቷል አትበሉን። በፈለጋችሁት ጊዜ ድሃውን ገበሬ ከመሬቱ እያፈናቀላችሁ የምታባርሩትና በሊዝ ስም ከባለሃብቶች እየተስማማችሁ ለግል ጥቅማችሁ የምታውሉት እናንተ አይደላችሁም? በማለት ሃሳባቸውን እንዳልተቀበለው ተገልጿል፣
     በመጨረሻም ተሰብሳቢዎቹ፣- ይህ በሃገራችን ያለው ድህነት ጠንቁ ያለፉት ስርዓቶች ናቸው የምትሉት። ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ወደ ስልጣን ከመጣ ብዙ ዓመታት አስቆጥሯል። ህዝቡን በአለፉት ስርዓቶች እያመካኛችሁ ለማታለል አትሞክሩ ድህነት በስብሰባና በምክንያት አይወገድም ሲሉ እንደተቃወሙት ለማወቅ ተችሏል፣