Tuesday, June 7, 2016

ልማት በውድመት አይረጋገጥም!!



    መሬት ለአንድ አገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የተፈጥሮ ሃብት መሆኑ የሚያጠያይቅ  ጉዳይ አይደለም።ይህንን ከተፈጥሮ የተቸረን ፀጋ ዜጎች እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ፤በፍትሃዊ ተደራሽነት የመሬት ባለቤት ሆነው፤ምርት አምርተው እንዲጠቀሙ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት እንደ ዋና መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት በመወሰድ መጠለያ አግኝተው የተረጋጋ ኑሮ እንዲመሩ የሁሉም ፍላጎት ነው ።
    በዘርፉ የመሬትን ጉዳይ ስንመለከት በአገራችን የመሬት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለዘመናት መፍትሔ ያላገኘ ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ትጥቅ አንስቶ ደማዊ ጦርነት ለማካሄድ ያስገደደው ምክንያት ከሃገሩ የተፈጥሮ ሃብት የመሬት ባለቤትነት አጥቶ ውስን ጨቋኝ መሳፍንቶች ይጠቀሙበትና ይበዘብዙት ስለነበር በትግሉ መክቶ የመሬት ባለቤትነቱንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ሲል ከባድ መስዋዕት ለመክፈል ተገዷል።
    ይሁን እንጂ በከዳተኛ የህወሃት ኢህአዴግ አመራሮች ምክንያት ህዝባችን የታገለላቸውን አላማዎች ወደ ጎን በመተው በግላዊ ጥቅማቸው ለውጠውታል።ዛሬ አምራቹና  ወጣቱ ኃይል ተገቢ የሆነ የመሬት ባለቤትነት ተነፍጎት በአገሩ መሬት አርሶ በማምረት ኑሮውን የሚመራበትና የሚያሻሽልበት ምቹ ሁኔታ ሊያገኝ አልቻለም። በተመሳሳይም የበሬ ግንባር የምታክል የታደላትን ቁራሽ መሬትም ቢሆን ከአቅሙ በላይ ግብር እየከፈለ መግቢያቸው የማይታወቅ ብዙ ወጭ እንዲከፍል እየተገደደ ከእጅ ወደ አፍ የሆነችውን ኑሮውን እንኳን ለመምራት ተስኖት በእዳ ውስጥ ተዘፍቆ ይገኛል።
    የአገርንና የህዝብን ሃብት መሟጠጥ የለመዱ አመራሮች በገጠርም ይሁን በከተማ የደም  ላብ አንጠፍጥፎ የሰራውን መኖሪያ ቤቱን ለልማታዊ ባለሃብቶችና ለተቋሞች ወዘተ በሚል ሽፋን በዶዘር እያፈረሱ ህዝብ ያለበቂ ካሳና ተለዋጭ መሬት ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጦ ለሚያቀርባቸው አቤቱታዎችና ጥያቄዎች ቀልጣፋ ምላሽ አጥቶ ሲንገላታ ማየት የተለመደ ነው።
    አንድ አገርንና ህዝብን አስተዳድራለሁ የሚል ስርዓት ግን የድሆችን መሬት ከመንጠቁና ቤቶችን ከማፍረሱ በፊት የሚኖረውን ጥቅምና ተጠቃሚነት ከህዝቡ ጋር ተረዳድቶ በቂ የሆነ ካሳ መጠለያ ቤቶችና ተለዋጭ መሬት በተገቢው መንገድ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።ፀረ ህዝቡ የህወሃት ኢህአዴግ ስርዓት ግን  ይህንን ለማድረግ ህሊናቸው ሊፈቅድላቸው ይቅርና ያለ በቂ ካሳና ተለዋጭ መሬት ቤታችን እንዲፈርስ አንፈቅድም መሬታችንን አንነጠቅም በማለት ወደ አደባባይ የወጡ ወገኖች የጥይት እራት ሆነዋል ።ያለፍርድ አሰቃቂ ግርፋትና እስራት እየወረደባቸው እንዲሰቃዩ እያደረጉ መጥተዋል አሁንም እየፈፀሙ ይገኛሉ።
   ሩቅ ሳንሄድ ባለፈው ሳምንት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማና በማይካድራ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ የድሃ ቤቶች በመውደም ላይ ይገኛል። ይህ በህወሃት ኢህአዴግ ባለስልጣናት ትዕዛዝ እየተካሄደ ያለው የቤቶች ማፍረስ ዘመቻ መፍትሄ አጥተው ሳይሆን የህዝብን መሬት ለውጭ ባለሃብቶች በመሸጥ ኪሳቸውን ለማሳበጥና ስስትነታቸውን ለማርካት መሰረት ያደረገ ነው።
    እነዚህ በስግብግብነታቸው አይናቸው የጨለመ ኢህአዴጋውያን በስልጣን እስካሉ ድርስ ከፀረ ህዝብ ተግባራዊነታቸው ተቆጥበው መፍትሄ የምንጠብቅ ከሆነ በህዝብና በሃገር ላይ ጥፋትና ውድቀት እየባሰ የሚሄድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።ስለዚህ ተገቢ ካሳ፤ጥናትና መረዳዳት ያልተደረገበት የመሬት ንጥቂያና ቤቶችን የማፍረስ ተግባር ውጤቱ ውድመት እንጂ የሚያመጣው ልማት የለም።




No comments:

Post a Comment