Tuesday, June 21, 2016

በውቅሮ ከተማ በኤሌክትሪክ ገመዶችና ፓሎዎች መንስኤ በሚከሰተው አደጋ የዜጎች ህይወት አሰቃቂ በሆነ መንገድ እየጠፋ እንደሆነ ተገለፀ።



   ሰኔ 10-2008ዓ.ም በውቅሮ ከተማ ደንጎሎ መናፈሻ በተባለ አካባቢ ባጋጠመ የኤሌክትሪክ ገመድ የመበጠስ አደጋ፣ 6 ሴቶችና ፤3 ወንዶች በጠቅላላ 9 ሰዎች በቅፅበት ህይወታቸው ሲያልፍ፣ አንዲት ህፃን አዝላ የነበረች እናት ደግሞ ከከባድ አደጋው በህይወት መትረፏን ለማወቅ ተችሏል።
   ይህ አደጋ በከተማዋ  ቀላል ዝናብ እየዘነበ በነበረበት ጊዜ ሁለት ፓሎዎች በመውደቃቸው ባስከተለው የኤሌክትሪክ ገመድ መበጠስ ያጋጠመ አደጋ ሲሆን፣ በሁኔታው የውቅሮ ከተማ ህዝብ በጣም እንዳዘነና አሁንም ቢሆን የኤሌክትሪክ ገመዶችና ፓሎዎች ዋስትን ሊሰጥ በሚችል መልኩ ተገቢ የሆነ ጥገና ስላልተደረገለት አደጋው ዳግም እንዳይከሰት ህዝቡ በከባድ ስጋት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
   እንደዚህ ያለ አደጋ ባለፈው ወር ከውቅሮ በስተምዕራብ አቅጣጫ በምትገኝ በዓቲ ዓኮር በተባለች ቀበሌ በኤሌክትሪክ መቃጠል አደጋ ምክንያት አራት ሰዎች በቀጥታ ሲሞቱ፣ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ደግሞ በከባድ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል እንደገቡ የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ አደጋዎች በመብራት ሃይል ትራንስፎርመሮችና የኤሌክትሪክ ገመዶች ብልሽት እንዲሁም ፓሎዎች እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው በሰዎች ህይወትና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ ያገኘነው መረጃ አስረድቷል።
   በውቅሮ ከተማና በአካባቢዋ የሚገኝ የመብራት ሃይልና መሳሪያዎቹ አራት ሚሊዮን ዶላር የተከፈለበት ሲሆን ይህ ደግሞ ጥራት የሌለው  በመሆኑ የገንዘብ ኪሳራና በዜጎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነና በዚህ ደግሞ የወያኔ ስርዓት ተጠያቂ እንደሆነ የተለያዩ ወገኖች በመግለፅ ላይ መሆናቸውን ተገልጿል።

No comments:

Post a Comment