Thursday, November 24, 2016

የእንበላሽ መድረክ



የህወሓት መሪዎች እንዳይራቡ አጥግቦ፣ እንዳይራዙ አልብሶ፣ እንዳይበርዱ በቤቱና በጓዳው አስገብቶ ያሞቃቸውንና ተንከባክቦ ያሳደጋቸውን የትግራይን ህዝብ ከድል በኋላ፣ የመስዋዕቱና የስንክልናው ፍሬ ከንቱ ሆኖ፣ ለወያኔ ኢህአዴግ አመራሮች የስልጣን እድሜ ማራዘሚያና ትናንት ሲያርዱት የነበሩትን አመፀኞች ጥቅም መደጎሚያ እንዲውል ማድረጋቸው የሚታወቅ ነው።
የትግራይ ህዝብ ከማንም በላይ ደምቶና ተሰንክሎ የተከለው ስርዓት ከማንኛውም ህዝብ በላይ ጥቅሙንና ተጠቃሚነቱን እንዲያጣ፤ እንዲደኸይ፤ ፍትህ እንዲናፍቀው፤ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ እንዲዘጋ፤ እንዲጠላ፤ ሐሳቦቹን የሚገልፅበት ነፃ መድረክና ሚዲያ ለማግኘት ያልታደለ በድርብ ጭቆና የሚሰቃይ ህዝብ እንዲሆን ደግሞ የህወሃት አመራሮች ታሪክ የማይረሳው በደል እየፈፀሙ መጥተዋል።
ዛሬ የትግራይ ህዝብ ወኪል ነን የሚሉት የህወሃት አመራሮች፣ ለፈፀሙት ክህደትና አሁንም በህዝቡ ላይ እያወረዱት ያሉት ሰይጣናዊ ተግባራትና በደል እንዲሁም በምክንያታቸው የተለኮሰ ሰደድ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰው ያለው በደልና ስቃይ ወደፊትም በጥቅላላ በኢትዮጵያ ጭቁን ህዝብ ላይ በተለይ ደግሞ በትግራይ ህዝብ ላይ አንጃቦ ያለውን አደጋ ለመከላከል፣ ህዝብ እንደ ህዝብ ዋስትናና ዘላቂ ጠቀሜታ የሚያገኝበትን ተግባሮች ማመቸቸት ትተው፣ ለህላዌ ስልጣናቸው ዋስትና በየጊዜው ስፍር ቁጥር የሌላቸው መድረኮች እያዘጋጁ ሞደል አርሶ አደር፤ ሞዴል ሰራተኛ እያሉ በሚያድሉት ሽልማት ህዝብ ሲያደናግሩና ቁማር ሲጫወቱ ቆይተዋል።
የዚህ ተከታይ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ማለትም ህዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም “የሃብት አስተዳደር ልማታዊ ሰራዊት በመገንባት የህዳሴያችንን ጉዞ እናደላድል” በሚል መሪ ቃል በእቅድና ፋይናንስ ቢሮ የተዘጋጀ ብልሹ መድረክ ሲያካሂዱ ታዝበናል። የዚህ ሽልማት አላማ ክልሏን እያመሰ ካለው አባይ ወልዱ እንደሰማነው፣ በእቅድና ፋይናንስ ቢሮ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ባስመዘገቡት የጠራ አሰራርና ህዝባዊ ወገንተኛነት መሰረት የእውቅና ሽልማት የሚሰጥበት ነው ቢሉንም እንኳ ዋና አላማው ግን የእንበላሽ መድረክ ነው የነበረው።
ይህ ደግሞ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች የክልላችንን የትግራይን ሀብት በልተው ስለቦረጩ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ስለተረዳቸውና ለእነዚህ ደህና የሆነ አሰራር ያቆዩትን ጥቂት የህዝብ ልጆች እኛ በልተን ጠግበናልና ትራፊያችንን ተካፈሉ በልታችሁ ደግሞ አፋችሁን ያዙልን። በአጠቃላይ አብረን እንበላሽ የሚል መልእክት ያዘለ መድረክ ነበር።
እርግጥ ነው እቅድ ስንል አንድ አገር የምትጓዘውን ርቀት የሚገልፅ ነው። ያለ እቅድ የሚመራ የሆነ ይሁን ስራ ግን ከቶውንም ለስኬት አይበቃም። ያለ እቅድ የምትመራ ሃገር  ደግሞ በዋናነት እንዴት እንደምትወድቅም አታውቅም። የህወሃት አመራሮች ደግሞ በእቅድ እየተመራን ነው ሲሉን ሳይገርመን አላለፈም። ትግራይ በእቅድ የምትመራ ብትሆን ኑሮ በትግራይ በአሁኑ ወቅት ያልቃሉ ተብለው ታቅደው የተጀመሩ ግን ደግሞ አንድ እርምጃ ወደፊት ሳይሄዱ ከእቅድ ውጭ አቅጣጫቸው ጠፍቷቸው ያሉ ተጀምረው የተቋረጡ ስራዎች ስንትና ስንት ናቸው።
ዛሬ በትግራይ ተጀምሮ የተጨናገፈ ከፍፃሜ ያልደረሰ ስራ አለን እያሉ የማያማርሩ ቀበሌዎች የሉም። እውነታው ይህ ከሆነ እነዚህ በሰማእታት ሃውልት አዳራሽ ከተለያዩ የትግራይ ቀበሌዎች እንደመጡና የተወከሉ ናቸው ተብለው፣ ከህዝብ ጋር ከመወገንና ማገልገል የሚበልጥ ዋጋ የለም፤ ለህዝብ የወገነ ከህዝብ አፍ ሊቀማ ወደ ሙስናና ብልሹ አሰራር አይገባም። የሚል ምክር እየተሰጣቸው ከቅድሳን ነጋ እና ከአባይ ወልዱ እጅ የስራ ጥራት የምስክር ወረቀት፤ በአንገት የሚንጠለጠል ብረትና ገንዘብ ሲሸለሙ የዋሉ ሰራተኞች እስኪ በየትኛው ቀበሌ ነው ሲሰሩ የነበረው? ከተባለ የትግራይ እቅድና ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ጽጋብ ማስራጃ ያለው መልስ ሊያቀርብ አይችልም።
አባይ ወልዱ በመድረኩ ተግኝቶ በእንዲህ አይነት የህዝብ ልብ ለመንካት በእንቁልምጫ ቃላት ዲስኩር አሰምቶ ነበር። “በንቃት ታግሎ ከባድ መስዋዕት የከፈለ ህዝባችን የትናንትና የዛሬ ጠላቶቻችንን ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር ሩቅ ተመልክቶ አመዛዝኖ በተሞክሮው ትግሉን እያካሄደ ያለው ህዝባችን ድርጅታችንንና መንግስትን በሁለት እጁ ደግፎ ተንከባክቦ አጠናክሮ ያለው ህዝባችን ከነበሩን ጉድለቶች ተላቀን ልንክሰው ፋይዳ እንዲያገኝ እንድናደርገውና ከልብ ወስነን የምንሰራበት ጊዜ አሁን በመሆኑ ይህንን ለመተግበር ዳግም ቃል ገብተን ልንዘምት ልማፀናችሁ እወዳለሁ” የሚል ንግግር አቅርቦ ነበር። 
ህዝባችን ይህ ቃል ለ25 ዓመታት መድረክ በተከፈተ ቁጥር ተመግቦታል። ለመሆኑ ህወሃት እስከዛሬ የት ስለቆየ ነው፣ ለህዝብ የምንወግንበት ወቅት ዛሬ ነው እያለ ያለው፣ የህወሃት አመራሮች እንዲያው አስመሳይነትን ተሸፍነው ንግግር የማይጠግቡ ሆነው እንጂ ህዝባችንማ እራሳችሁ የፈጠራችሁትን አደጋና ያበላሻችሁትን አሰራር ዛሬ በእያንዳንዱ ሴክተሮች ያለውን አባላችሁን ና የጥጋባችንን ትራፊ ሰርቀን ካጠራቀምነው የህዝብ ገንዘብ እናቅምስህና አፍህን ዝጋልን ነው እያላችሁ ያላችሁት። ይህ ተንኮል አሁን ተፈጥሮ ላለው አደጋና ጥፋት አጋልጦናል፣ በተደጋጋሚ በሚደረግ የእንጨማለቅ መድረክ የሚደናገር ህዝብ የለም እያለ በጥብቅ እየተቃወመ ነው። የጭቁንን ድምፅ የሚሰማ ጆሮ አልታደለም እንጂ። 
ዛሬ ህዝባችን መድረክ ከፍቶ የሚጨፍርና ከአዳራሽ ሲወጣ የሚረሳቸውን መፈክሮች የሚደጋግም ድርጅት አይደለም እየፈለገ ያለው። ህዝባችን በጀት የለም እየተባለ ወራቶች አልፎ ለአመታት በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ከመሰቃየት የሚያላቅቀው፤ በመብራት ሃይል ችግር እየደረሰበት ካለው ተደራራቢ ችግር የሚፈታለት፤ ብሎም በአዋሳኝ ክልሎች ያለውን መፍትሄ ያጣ ጥላቻ ወደ ሌላው ትውልድ እንዳይሸጋገር መቋጫ ሊያደርግለት የሚችል፤ መልካም አስተዳደር በተግባር እንጂ በፉከራ አይሰፍንም የሚሉትንና ሌሎችንም መሰረታዊ ችግሮቹ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ለአመታት እያቀረባቸው የመጣውንና ያለውን ጥያቄዎቹ ያለዋል እደር ሊፈታለት የሚችል ህዝባዊ መንግስት ለመትከል ነው እየጠየቀ ያለው።
ይህ ደግሞ በቁሙ ሊቀበር ተዘጋጅቶ በእንበላሽ መድረክ ዘመቻ ተሰማርቶ ያለው የህዝብ ውክልና የተነፈገው የህወሃት አመራር መሰረታዊ ለውጥና መፍትሄ ያመጣል ተብሎ የማይታሰብ ስለሆነ፣ በሚያካሂዳቸው የቀቢፀ ተስፋ ተግባሮች ሳንደናገር ሁላችንም ለውጥ ፈላጊ የሆነ ጭቁኖች በአንድ ላይ በመተባበር የጥፋት ጎዳና ሳይቀድመን የለውጥ ጎዳና ልናስተካክል ይገባል።

No comments:

Post a Comment