Friday, December 9, 2016

“የለውጥ እንቅፋት”



የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፀረ ህዝብ በሆነው የወያኔ ኢህአዴግ አስተዳደር ስር ወድቀው፣ ላለፉት ሩብ ክ/ዘመናት አሳርና መከራ በላያቸው ላይ ተጭኖ፣ እድገታቸው ተሰናክሎ፣ ድህነት ከጓዳቸው አልወጣ ብሎ፣ በችግር ላይ ችግር ተደራርቦባቸው ደስታቸው ተነጥቆ፣ ፍትህ አጥተው፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ርቋቸው፣ መልካም አስተዳደር በወያኔ ኢህአዴግ አመራሮችና ካድሬዎች የሙስና ተግባራት ተረግጦ ሃገርና ህዝብ ወደ ጥፋት ጎዳናና ውድቀት እያመሩ መጥተዋል።

   በህዝብ ገንዘብ ኪሳቸውን ያሳበጡ ጥቂት የወያኔ ኢህአዴግ ዘራፊ ቡድን ዛሬ ሰንሰለታቸውን ከ25 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያወረዱት አሰቃቂ ግፍ፣ ሲያታልሉት የመጡት ሁለመዳያዊ የማደናገር ሂደቶች፣ የሚታገስ የህዝብ ቦታ ይሁን ትግስተ ህሊና እንደሌለ ባረጋገጠበት ወቅት እንገኛለን። ምክንያቱም በዚህ በቅርብ ወራት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች በወያኔያውያን ላይ ያነጣጠረ የተነሳው ህዝባዊ አመፅ የውድቀታቸው ማሳያና የህዝብ ድጋፍ ማጣታቸውን የአምባገነን አስተዳደራቸው ውጤት ስለሆነ፣
የህዝብ እንቢተኝነት ማዕበል ተቀጣጥሎ ባለበት ጊዜ ለዚህ ስስታም ባህሪያቸውና የስልጣን ጥማታቸውን ላለመተው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከለላ አድርገው ከፌደራል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጀምሮ በውረድ ተዋረድ ስማዊ መቀያየር በማድረግ፣ በክልሎችም በተመሳሳይ ጨዋታ ተጠምደው የአዳዲስ አባላት ስም ከአቶ ወደ ዶክተር ሲሸጋገር እየታዘብን ነው።

ለምሳሌ የሌሎች ክልሎች ድርጅቶችን እንደተመሳሳይ ወስደን ህዳር 26 ቀን 2009 ዓ.ም በትግራይ የተካሄደውን ጨዋታ ማየት ይቻላል። በዚህ መሰረት የትግራይ ህዝብ እነዚህ ለዚህ ሁሉ ችግር ያበቁት የህወሃት አመራሮች ዛሬ ታሪክህ ይፃፍልሃል በሌላ በኩል ደግሞ በሙስና ቆይተን በድለንሃል የህዝብ ጫማ ሆነን ህዝባችንን የምንክስበት ጊዜ አሁን ነው በማለት ይገኛሉ።

በጥልቀት ታድሰን የአመራር ለውጥ አድርገንልሃል በማለት እያካሄዱት ያሉት የዘወትር መዝሙር፣ መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ እየጠበቀ ያለው ህዝባችን፣ የህዝባዊነት ለዛ የሌለውና የሰማዕታትን አደራ ረስቶ የአገርና የህዝብን ሃብት ለብቻው እየሟጠጠ በሙስና የተጨማለቀ አመራር፣ ጥቂቶች ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ያልቀመሱት ቢሮ ቀይረው ምሁራን አስገብተናል በማለት ለውጥ ለማምጣትና ህዝባችንን ልንክስ ነው በማለት ሲምሉና ሲገዘቱ ተመልክተናል።
 
    የትግራይ ህዝብ ግን ለ17 ዓመታት ህይወቱንና ንብረትን በሙሉ ገብሮ ከሌሎች የአገሩ ህዝቦች ጋር መተኪያ የሌለው መስዋዕት ከፍሎ ለድል ሲበቃ፣ በጀርባው ታዝለው ወደ ስልጣን የወጡት ጥቂት የህወሃት ባለስልጣናት እንደመዥገር በደሙ ተጣብቀው የሰማዕታትን አደራ ረግጠው፣ በጎስቋላ ኑሮና ድህነት ተዘፍቆ ረድኤት እየጠበቀ፣ ፍትህ በገንዘብ ሲሸምት፣ መብቱ ታፍኖ በህወሃት ጥብቅ ጥበቃና ክትትል አደረጃጀት ወድቆ በአጠቃላይ በስሙ እየማሉና እያላገጡ ለዘላለም ደሙን እንደሚመጡት አልጠበቀም።

ይሁን እንጂ “እናትና ልጅ ሃዘናቸው ለየብቻ” እንደሚባለው ሆኖ የትግራይ ህዝብ የሚጠብቀው ለውጥ ሌላ ህወሃት የሚያደርገውና የሚያበላሸው ደግሞ ሌላ እየሆነ ሩብ ክ/ዘመን ተቆጥሯል።
በተመሳሳይ የምናነሳው ጉዳይ ካለ፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሚል ምክንያት በሐረር ክልል ለ11ኛ ጊዜ “ሕገመንግስታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል የህዝባዊነት አንደበት በሌላቸው ሚዲያዎች በኩል መሬት ላይ የሌለውን ምስል ሲያደምቅ ሰንብቷል።

ይህ በኢትዮጵያ ህዝቦች ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሽፋን ለፕሮፖጋንዳ ሴራና ተንኮል ሆን ተብሎ የተቀመረ የኢህአዴጋውያን መሳርያ በመሆኑ፣ ዛሬ በሁሉም የአገራችን ማዕዘናት ጭቁን ዜጋ እያነሳው ያለው የፍትህ፤ የመልካም አስተዳደር፤ የልማት ጥያቄ፤ የማንነት ጥያቄ፤ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ወይም በልዩ ዞን የመተዳደር ጥያቄ በአዋሳኝ ክልሎች የሚነሱ መፍትሄ ያጡ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄና ሰላም ለማግኘት ለዓመታት ያህል እያቀረባቸው የመጣና ያለ ጊዜ የማይሰጡ ጥያቄዎች መፍትሄዎችን ከማስቀመጥ ይልቅ መልሱ ፀረ ሰላምን ፀረ ህገ-መንግስት እየተባለ መታሰር መደብደብና መገደል እጣው ሲሆን ተገዶ ወደ አመፅና ግጭት መግባቱ የሚታወቅ ነው።
   ለዚህ ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው የህገመንግስቱን ድንጋጌ እየጣሱ መምሪያዎችን እያወረዱ በየቀኑ በፀጥታ ሃይሎች የሚፈፅሙት ግርፋት፤ እስራት፤ ግድያ፤ ረስተው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ብለው የለውጥ እንቅፋት ቢፈጥሩ የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም የፀረ ህዝብ ስርዓት ባህሪና ተግባር ስለሆነ።

No comments:

Post a Comment