Saturday, January 14, 2017

ጭንቀት የወለደው ድንግርግር



ይህ ከ25 ዓመታት በላይ የህዝብን ትግል በሃይሉ ቀምቶ የአገራችንን ህዝቦች የደም እንባ እያስለቀሰ ያለው የወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ከሱ በፊት ከነበረውና ለ17 ዓመታት ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች ካስከተለው አምባገነናዊ የደርግ ስርዓት ጋር ህዝብ የሁለቱንም ዓመፀኞች ስርዓት ባህርያት አነፃጽሮ የተመለከተበት መድረክ ደርሷል።

ማለትም ኢህአዴግ በእነዚህ የሩብ ክፍለ ዘመን እድሜው፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር እየፈጠረው ያለው ረጅም ተጓዥ እኩይ ተግባሮቹን ትተን፣ በኢትዮጵያ ህዝቦች ደም ተከፍሎባት የጨበጣት መንበረ ስልጣኑ ከእጁ እንዳትወጣ፣ እንደ ተቆርቋሪና የስልጣን እድሜው ማራዘሚያ አድርጎ እየሰራባት ያለው ተንኮል፣ የኢትዮጵያን ብሄር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እርስ በርሳቸው እንዲበላሉ በማድረግ በመካከላቸው አስታራቂ መስሎ ማለቂያ የሌላቸው የፀጥታ ሃይሎቹን እያሰማራ በንፁህ ዜጋ ላይ ወጥመድ እያጠመዱና ንፁሃን ወገኖቻችን እንዲታሰሩና እንዲጠፉ እያደረገ መጥቷል። አሁንም እያደረገ ይገኛል።

እንደዚህ አይነቱ የወለደው ደግሞ ሰፊ ንቅናቄ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በየግዜው ከአገራችን ከተሞች እስከ ከገጠር እየተቀጣጠለ ሊያገግም ባለመቻሉ ትጉሃን ሰዎች በሁሉም አካባቢዎች እየሰረጉ በድፍረትና በቆራጥነት ስለፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፤ እኩል ተጠቃሚነትና ልማት ሲሉ ፊት ለፊት ለወያኔ ኢህአዴግ ጥይት ግንባራቸውን ሰጥተው ህይወታቸውን ለማጣት ተገደዋል።  

ይህ በኢትዮጵያ ህዝቦች የተነሳው ትንፋሽ የማይሰጥ ዓመፅና የለውጥ ትግል በአንድ በኩል ስርዓትን ከሞት አፋፍ ስር ያደረሰ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ከሐዲ ስርዓት ለአመታት በላዩ ላይ ሲፈፀምበት የቆየውን አንገፍጋፊ በደሎች፤ ብዝበዛና ስቃይ ይበቃል ብሎ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያነሳሳውና ያቀጣጠለው ትግል ግቡን ሊመታ የሚችል የተደራጀና የተጠናከረ ኢትዮጵያዊ ክንድ የሚሻበት ወቅት ላይ መሆናችን ደግሞ የግድ ሆኗል።
ይህ ፀረ ህዝብ ስርዓት በመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች እየተካሄደ ላለው በላዩ ላይ ያነጣጠረ ተቃውሞና ዓመፅ መፍትሔ ሳይሰጠው፣ ጭንቀት በወለደው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ቆርፍዶ በመያዝ፣ ነጋ ጠባ ለመንበረ ስልጣኔ ከለላ ይሆኑኛል ብሎ ወደ መላ የአገራችን አካባቢዎች ያሰማራቸው የፀጥታ ሐይሎችና የመከላከያ ሰራዊት መብቴን ብለው የጠየቁ ንፁሃን ወገኖችን እየፈለገ ሲያስርና በማሰቃየት ላይና ታች ሲል ይታያል።
ይህ ደግሞ ስርዓቱ በአሁኑ ወቅት የአስተዳደሩና የእንቅስቃሴው ቀልብ ጠፍቶት በከፍተኛ ጭንቀትና ቀውስ ተውጦ የሚይዘውና የሚጨብጠው ባጣበት ሁኔታ እንዳለ የሚያመላክት ከመሆን አልፎ ይህ ነው የሚባል የመፍትሄ ሃሳብና ተግባር እንደማያመጣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በትኩረት በማየትና በመመልከት በቂ መረጃ ለማግኘት  ይቻላል።

ምክንያቱም ስርዓቱ ከስህተቶቹ ታርሞ፣ በህዝብና በአገር ላይ አንጃቦ ካለው አደጋ የሚያድን ዘላቂ መፍትሔ ከማስቀመጥ ይልቅ፣ ለእንደዚህ አይነት አደጋ የሚያጋልጡትን ተግባራትና የማታለያ ስልቶቹን ተከትሎ፣ አታስፈልገንም በማለት ለተነሱ ሊገቱ የማይችሉ ህዝባዊ አመፆች በታዩበት አካባቢዎች መርዝ የላሱ የበቀል ቃላት ለማሰማት ባልተገደደ ነበር።

በመሰረቱ ግን ህዝባችን እነዚህ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ማለቂያ የሌለው ግፍና ሰይጣናዊ ተግባራት ሲፈፅሙ የቆዩ አካላት፣ አሁንም ቢሆን ይዘውት ከቆዩት መስመር ወጥተው ህዝባዊነት ሊላበሱና ለዚህ ተፈጥሮ ላለው አደጋና ውጥረት መፍትሔ ያስቀምጡለታል የሚል እምነት የለውም።

በዚህ ምክንያት ደግሞ ስርዓቱ በዚህም አለ በዚህ፣ ራሱ ከፈጠረው አዘቅት ይወጣል ተብሎ የሚታሰብ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ከህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎት ወጥቶ ውሸትና ማታለልን እንደ አሰራር ወስዶ እየናፈቃት ባለው ስልጣን ለመቆየት እየተፍጨረጨረ ያለ ቢሆንም፣ ህዝብ ግን ይህ መጥፎ ተግባራችሁ ይበቃናል ከማለት ውጭ ሌላ ጉጉት አላደረገበትም፣

ስለዚህ ስርዓቱ በጭንቀት ተወጥሮ እያደረጋቸው ባለው ድንግርግር እንቅስቃሴዎች ሳንደናገር ለዚህ መድሃኒት ላልተገኘለት ቀውስ ፍትህና ዴሞክራሲ ፈላጊ የሆነ ኢትዮጵያውያን ይህንን ፀረ ህዝብና ሃገር የሆነ ስርዓት ከስሩ ለመንቀል በአንድ ላይ ልንተባበር ይገባል።

No comments:

Post a Comment