Sunday, February 26, 2017

የካቲት 19 የድርጅታችን ትህዴን 16ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የተሠጠ ድርጅታዊ መግለጫ!!



የተከበርክ በውስጥና በውጭ የምትገኝ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የተከበርክ ጀግናው የት.ህ.ዴ.ን ተጋይ፣ የተከበራችው በውስጥና በውጭ የምትገኙ የድርጅታችን ስቢል ኣባላት፣ ድርጅታችን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ት.ህ.ዴ.ን/ ጭቁንነት ባንገፈገፋቸው፤ የአምባገነኖችን የባርነት ቀንበር ባልተቀበሉ፤ የህዝባቸው ብሶት በሚሰማቸው የህዝብ ልጆች ልክ በዚህ ሰሞን በየካቲት 19 ቀን 1993 ዓ.ም የነፃነት መባ ለመሆን በረሃ ወጥተው ሲመሰርቱት ወቅታዊና ፍትሃዊ ስለነበር ብዙ ተከታዮችን አግኝቶ ዓበይት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስራዎችን እየፈፀመ ነው እዚህ ደረጃ ደርሶ ያለው።

ድርጅታችን ከነሐሴ 28 ቀን እስከ ጳጉሜ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ባካሄደው ስኬታማ 2ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የነበሩንን ውስጣዊ ደካማ ጎኖችና ጠንካራ ጎኖች ለይተን፤ የጠላታችንን ሁኔታ ደግሞ በጥልቀት በመገምገም ለቀጣይ ሊያሰራን የሚችል እስትራቴጂ ነድፈን በአስተማማኝ ደረጃ ሆነን የትግል ጉዟችንን ወደ መጨረሻው ድል ለማድረስ በፍጥነት በመገስገስ ላይ እንገኛለን።
ት.ህ.ዴ.ን እንደ ድርጅት እስካሁን የሰራቸው ስራዎች የትኞቹ ናቸው? ሊሰራቸው ከሚገባው ያልተደረሱ ወይም ያልተጨበጡ ድሎችስ የትኞች ናቸው? ለቀጣይስ በምን ዓይነት እስትራቴጂ ከተጓዝን ነው ወደ ሙሉ ድል ደርሰን ህዝባችን ካለው ጨፍላቂ ስርዓት አርነት አውጥተን የተመቻቸ ህይወት ለመምራት እንዲችል የሚል በጥልቀት ገምግመን በ2ኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን የነደፍናቸውን የትግል እቅዶች ከግባቸው ለማድረስ ቀን ከሌት በኃያል ጥረት ላይ እንገኛለን።
ብዙ ወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግን የሚታገሉ ድርጅቶች በሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ከስልጣኑ ይወገዳል ብለው ወስነው ሰላማዊ ትግል ያካሂዱ በነበሩበት ወቅት፣ ት.ህ.ዴ.ን የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት በትጥቅ ትግል እንጂ በሰላማዊ መንገድ ከስልጣኑ ሊወርድ አይችልም የሚል አቋም ይዞ አማራጭ የሌለው መፍትሄ የትጥቅ ትግል እንደሆነ ሲወስን ደግሞ ልክ አሁን እየታዘብነው እንዳለነው ስርዓቱ አምባገነናዊነቱን እያስፋፋ እንደሆነ አስቀድሞ ስለ አወቀው ነበር።
ይህ አሁን በስርዓቱ በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለው አሰቃቂ በደል ደግሞ ለድርጅታችን ት.ህ.ዴ.ን ከ16 ዓመታት በፊት ግልጽ ስለነበር፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይህን አረመኔያዊ ስርዓት ለማስወገድ የመጨረሻ መፍትሄው የትጥቅ ትግል ነው ብሎ አስምሮበት ያለፈ ጉዳይ ነው። የወቅቱ ውሳኔያችን ትክክለኛና የማያሻማ እንደነበረ ደግሞ በዚህ በአገራችን አጋጥሞ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ አረጋግጠናል።
የተከበርከው የኢትዮጵያ ህዝብ፦ የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ እያወረደው ያለው አፈናና ረገጣ፤ ግድያና እስራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣት ዛሬ የመጨረሻ ጫፍ ላይ ደርሶ ልትታገሰውና ልትቋቋመው በማትችለው ጫፍ ደርሶ ይገኛል። የዚህ ውጤት ደግሞ በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በስርዓቱ ላይ እያደረግኸው ያለኸው አመፅና ንቅናቄ በጣም የሚያኮራ ነው። እንደውጤቱም ስርዓቱን አናግቶ ከውድቀቱ ጫፍ ላይ ደርሶ ይገኛል።
የወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት በስልጣን ኮረቻ ላይ ተኮፍሶ ህዝባችንን እየበዘበዘ ለመቀጠል የዘላለም ምኞቱ ስለሆነ ስልጣኑን እንዳያጣ ሲል ብዙ እንቅፋቶችን እየፈጠረ ነው የሚገኘው። የዚህ ማሳያ ደግሞ ህዝባዊ አመፆችን ለማስቆም ብሎ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህዝብ እንደ ህዝብ፤ ሃገር እንደ ሃገር አጥር የሆኑ መምሪያዎችን አውጥቶ ቆርፍዶ በመያዝ አራጊ ፈጣሪ ሆኖ ቸፈረሴ ለማለት ያሰበው ወጥመድ ወደ ራሱ እንዳይገለበጥ ላይ ታች ሲል ይታያል። ይሁን እንጂ ይህ ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ከጥቂት የቴክኒክ እጥረቶቹ በስተቀር ትክክለኛ የለውጥ መንገድ ነው የነበረው። ለህዝብና ለአገር አደጋ ሆኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅበት ምክንያት አልነበረውም። አደጋ ሊሆን የሚችለው ለፀረ ህዝቡ ስርዓት ብቻ ነው። ይህ አዋጅ ደግሞ አገራችንን እንደ አገር የህግ ሽፋን ተጠቅሞ ህጋዊ እስርቤት ለማድረግ ያለመ ነው። በዚህ የተነሳ ደግሞ ህዝብና በስልጣን ላይ ያለው ገዥው  ስርዓት ሙሉ በሙሉ ሊነጣጠሉ ችለዋል።

ይህ ስርዓት ህዝብ አንድ ሆኖ በላዩ ላይ ተነስቶ እንዳለ ሙሉ መረጃ ስለያዘ ይህንን ህዝብ አንድነቱን እንዳልነበረ ለማድረግ ከፋፍለህ ግዛ የሚል እኩይ እስትራቴጂ በተግባር በማዋል በግልፅና በድብቅ ህዝባችንን በታትኖ ሃይሉን ለማዳከም ሳይሰለች እየሰራ ነው። በሆዳቸው ባደሩት ካድሬዎቹ ተጠቅሞ እስከ ቀበሌ እየወረዱ አንድ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ ጥቃት እንዲያውጅ መነሳሳት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ።
እንደውጤቱ ደግሞ በአንዳንድ ወገኖች በትግራይ ህዝብ ላይ እየወረደ ያለው ብሄርን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከባድ የአካልና የህሊና ቁስል ፈጥሯል። ብዙ ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ፤ ለአመታት ከርተት ብለው ያፈሩት ንብረታቸው እንዲቃጠል፤ ይኖሩበት ከነበሩት አካባቢዎች በሃይል ተባረው ንብረታቸውንና ቤታቸውን ትተው እንዲወጡና ባዶ ሜዳ ላይ ተወርውረው ለፀሐይና ለንፋስ ለተለያዩ ህመሞች ሊጋለጡ ችለዋል።
ስለዚህ የዚህ መነሻና ተጠያቂው ወያኔ ቢሆንም እንኳ የተለያየ ሽፋን ተጠቅሞ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ተቀባይነት ስለሌለው፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አጥብቆ ይቃወመዋል፣ ይኮንነዋል። የት.ህ.ዴ.ን ድርጅት ለህዝብ ብሎ ከባድ መስዋዕት እየከፈለ ያለ ህዝባዊ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተቃራኒ የታጠቁ ሃይሎችን በህዝብ ላይ መጥፎ እርምጃ የሚወስዱ ሰወችን ደግሞ ከስርዓቱ ለይቶ እንደማያያቸው ያስጠነቅቃል። ስለዚህ ሁላችን ኢትዮጵያውያን ከጠባብነትና ከትምክህት ወጥተን የትግላችን ኢላማ በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ላይ ብቻ ማነጣጠር እንዳለበት ት.ህ.ዴ.ን ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበርህ ሕዝባችን፦ በዚህ ባለፈው አመት 2008 ዓ.ም ጀምረህ እስካሁን በከባድ ድርቅና የስርዓቱ ብልሹ አስተዳደር በሁለት አለንጋ እየተገረፍክ እያሳለፍከው ያለኸው ህይወት ለድርጅታችን ት.ህ.ዴ.ን የሚያሳዝን ፍፃሜ ነው። እነዚህ እንደ ጅብ ቁስላቸውን እየበሉ የሚሄዱ መሪዎች ነን ባዮች ግን፣ በድርቅ ስም ከውጭ ሃገሮች ለሚያመጡት ረድኤት አንተን በጉሮሮህ ይዘው የራሳቸውን ሞልተው እየጎረሱ በግላዊ ጥቅማቸው እያዋሉት መምጣታቸው እንዳይበቃ ድርቅ የሚቋቋም ኢኮኖሚ ገንብተናል፣ ድርቅ እንጂ ረሃብ የለም እያሉ ያልበላኸውን በላህ ሲሉህ እየሰማን ነው። ዛሬ በአብዛኛው የአገራችን አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ድርቅና የውኃ ጥም ተጋግዘው እየገረፉህና ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋልጠህ እየተሰቃየህ ቢሆንም ስርዓቱ ግን ይህንንም ሊደብቀው ነው እየፈተነ ያለው።
ስለዚህ ወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ባለፉት 25 ዓመታት በስልጣን ላይ ቢቆይም በአገር እድገትና በሕብረተሰቡ አኗኗር ላይ የሆነ ይሁን ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። በተቃራኒው ግን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እያፈነ፤ ዴሞክራሲ ብሎ የሚጠይቀውን ደግሞ በአደባባይ በግልፅ እየረሸነ፤ አስሮ እያሰቃየ፤ ለህዝባችን በጉቦና በአድሎ ቤቱን እየዘረፈ ወደ አስከፊ ድህነት ሊያስገባው ችሏል።
ስለዚህ ያለንበት ወቅት ከአለፈው ጊዜ በላይ የትግል ጊዜ ስለሆነ ጭቁንነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ወደ ከፋ ደረጃ ስለደረሰ የትጥቅ ትግል አማራጭ የሌለው የመጨረሻ አማራጭ መሆኑ የተረጋገጠበት ጊዜ ስለሆነ፣ ትግላችን ወቅታዊና ፍትሃዊ ነው ብለን አጠናክረን የምንቀጥልበት መሆናችንን ለማረጋገጥ እንወዳለን።
የተከበርህ የኢትዮጵያ ህዝብ፦ ይህ የአንድነትህና የእድገትህ ፀር በመሆን የተነሳውን ስርዓት ሙሉ በሙሉ ከስልጣኑ ተገርስሶ መውረድ ስለሚገባው ካለፈው ጊዜ በላይ አደረጃጀትና ትግል ይጠይቅሃል። እየተመኘኸው ያለኸው የዴሞክራሲ ለውጥ በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ፣ መጭዋን ኢትዮጵያ ከሚያለመልሙ ድርጅቶች ጋር ልትጣመርና ድርሻህን ልታበረክት የምትችልበት ጊዜ አሁን ነው። አገራችን ኢትዮጵያ በአደገኛ ቀይ መስመር ረግጣ እንዳለች ተረድተህ አገርህን ከመበታተን እንድታድናት ጊዜ የማይሰጥ አስቸኳይ የቤት ሥራ እንዳለብህ አምነህ ተነስ።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች፦ አሁን ያለው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት የፈጠረው በህዝባችን እየታየ ያለው መከፋፈልና ጥላቻ ወደ ነበረበት ሊመለስ ከሆነ፣ በዋናነት ደግሞ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስልጣኑ ሊወገድ ከሆነ እኛ የግድ በህብረት ልንሰራና ልባዊ መተጋገዝና ቅርርብ ልናደርግ ይገባል። የእኛ አንደነትና ውህደት ለኢትዮጵያ ህዝቦች ፍቅርና የጋራ እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ጉዞ ግን ስርዓቱን ካልሆነ በስተቀር ለማንም ሊጠቅም እንደማይችል ደግመን ልናሰምርበት እንወዳለን።
ይህ ወቅት አንድነትን የሚጠይቅ ወቅት ስለሆነ ድርጅታችን ት.ህ.ዴ.ን ለጋራ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም አስመልክቶ የመሰረተው ትግል ከግቡ ለማድረስ ከሁሉም በኢትዮጵያ አንድነት በሚያምኑ ታጋይ ድርጅቶች አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።

ድርጅታችን ት.ህ.ዴ.ን ይዞት ያለው ትግል ደግሞ ወቅታዊና ፍትሃዊ ስለሆነ ገና ስንመሰርተው እዚህ ደረጃ ላይ ይደርሣል ብቻ ሳይሆን፣ ለዚህ ፀረ ህዝብ ስርዓት ደምስሶ ሠላምና ዴሞክራሲ እንደሚያረጋግጥ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለንም። ስለዚህ ይህን ፍትሃዊ የህዝብ ትግል ከግቡ ለማድረስ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ጠንክረን እንታገላለን።

ለማጠቃለል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በውስጥና በውጭ ለምትገኙ የትግላችን ደጋፊዎች፤ ስለጭቁኖች ክቡር መስዋዕት እየከፈላችሁ ያላችሁ ጀግኖች የት.ህ.ዴ.ን ታጋዮች፣ እንኳን ለየካቲት 19 የድርጅታችን ት.ህ.ዴ.ን 16 ዓመት የምሥረታ በዓል በሠላም አደረሳችሁ እያልን፣ አጋምሰነው ያለነው 2009 ዓ.ም የድል ዘመን ይሆንልን ዘንድ ት.ህ.ዴ.ን መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖች ሰማዕታቶቻችን!!
ድል ለጭቁኖች!!
የካቲት 19 ቀን 2009 ዓ.ም





1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete