Saturday, February 18, 2017

በመረብ ለኸ ወረዳ ራማ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተውን በጥልቀት እንታደስ የሚል ስብሰባ ተከትሎ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች እንደታሰሩ ምንጮቻችን ገለፁ።



ከስብሰባው በኋላ በህዝብ ላይ ሲቀልዱ የቆዩት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሊያዙና ሊጠየቁ ህዝብ እየጠበቀ ቢሆንም እንኳ፣ በተቃራኒው ለዚህ ከለላ ሊሆንላቸው የሚችል ከፍተኛ ባለስልጣን የሌላቸው የታችኞቹ ሰራተኞች እንደታሰሩና እንደተባረሩ እየተገለፀ ነው።
በዚህ መሰረት ከዚህ በፊት ፖሊስ የነበረና በዚህ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በፀጥታ ፅህፈት ቤት ሲሰራ የነበረ ዘአብ የተባለ፤ ኪዳኔና ፍትሐነገስ የተባሉ የፋይናንስ ሰራተኞች የነበሩ፤ ፀጋይ የበሪሃ ቀበሌ ስራ አስኪያጅ የነበረ ሙስና ፈፅማችኋል ተብለው የታሰሩ ቢሆኑም እንኳ፣ ህዝብ ግን በዚህ ተግባር ደስተኛ እንዳልሆነ በመግለፅ ላይ ነው።
ያልተደሰተበት ምክንያት ደግሞ አሁን ከእነዚህ ታስረው ካሉት የታችኞች የመንግስት ሰራተኞች በላይ በህዝብ ላይ አሰቃቂ ብዝበዛ ሲያካሂዱ የቆዩና በሙስና የተዘፈቁ የወረዳዋ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ነፃ ስለተባሉ እንደሆነ ታውቋል።
ባለፈው ዜናችን ታላልቅ ዓሣዎችን ትቶ ትናንሽ ዓሣዎችን ለመዋጥ ያለመ ስብሰባ በከተማዋ እየተካሄደ እንዳለ መግለፃችን የሚታወስ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በራማ ከተማ ባለው ብልሹ የሆነ አስተዳደራዊ አሰራር የተነሳ ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እያጋጠመ እንዳለ ምንጮቻችን ከላኩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

No comments:

Post a Comment