Wednesday, March 22, 2017

ለፀፀት የሚዳርግ መልኩን የሚቀያይረው የዜጎቻችን ጥቃት ለወያኔ ኢህአዴግ ምኑም አይደለም



ይህ በአገሪቱ ላይ እየፈነጨ ያለው ጨፍላቂ ስርአት መብትንና ጥቅሞቹን ለማረጋገጥ እየታገለ ባለው ህዝብ ላይ ለመቀየስ እያካሄደው ያለው ተደራራቢ ግፍ ሳያንስ፣ አይነታቸውን በሚቀያይሩ አደጋዎች በህዝብ ላይ አሰቃቂ ጥቃት እስከሚደርሱ አድፍጦ ነው ያለው።   
   ይህ ስርዓት ከመሰረቱ ለህዝብ ዋስትና፤ ጥቅምና ፍላጎት የቆመ ሳይሆን የጥቂቶችን ጥቅም የሚያረጋግጥ ብዙዎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ጨቋኝ ስርዓት በመሆኑ፣ ህዝባችን በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮኣዊ አደጋዎች እየተጋለጠ ህይወቱን፤ ንብረቱንና ጥሪቱን እያጣ መጥቷል።
   በመሆኑም ይህ ስርዓት ለዜጎቹ ዋስትና የሚሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊያደርግ ባለመቻሉ በህዝብ ላይ በየጊዜው መልካቸውን እየቀያየሩ እየተከሰቱ ባሉት አደጋዎች የየራሳቸው ጥቁር ነጥብ እየተው ያልፋሉ።
   ይህ በየአመቱ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮኣዊ አደጋዎች የወገኖቻችንን ህይወት እየቀጠፉ እያለፉ ያሉት፣ የተለያዩ አደጋዎች እንደ ልማድ አድርገን በዚህ ወቅት ብቻ ይህ ስርአት እየተመራበት የመጣና ያለውን ሙሰኛ አስተዳደሩና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዱ የወለደው ትርምስና አሁንም አንጃቦ ያለውን አደጋ ተከትሎ አገሪቱ ራቁቷን የቀረችበት በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ያለው የዋጋ ውድነትና እየተከሰተ ያለው ተከታታይ ድርቅ በደሃ ህብረተሰባችን ላይ እያስከተለው ያለው የረሃብ አለንጋና የተጎሳቆለ አኗኗር የሚረሳ አይደለም።
   እነዚህ የየራሳቸውን መድረክ ይዘው እየተፈፀሙ ያሉት አደጋዎች በህዝብና በሃገር ላይ እያደረሱት ያሉት ቁስል ለመገመቱ የሚያስቸግር አይደለም። በተለይ ደግሞ ይህ ፀረ ህዝብ ስርዓት ከሃገሩ አልፎ የጎረቤት አገሮችን ሰላም ሊጠብቅ የሚችል ሰራዊት ገንብቻለሁ፣ አቋቁሜያለሁ ሲለው የቆየውና ያለው ፕሮፖጋንዳው መሬት ላይ እየወደቀ ብላሽ እየቀረ ነው።
   ምክንያቱም ይህ በሚያዝያ 2008 ዓ/ም ከደቡብ ሱዳን ተነስተው የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በጋንቤላ ህዝብ ላይ ጥቃት የፈፀሙ ጠመንጃ የታጠቁ ሃይሎች ከ200 በላይ ወገኖቻችንን የቀጠፉና ከ125 ህፃናት በላይ ሲያግቱና በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶቻቸውን ሲዘርፉ ተሯሩጦ ያዳናቸውና ለዜጎቹ ደህንነት ለመዋስ የታጠቀ ህዝባዊ ሃይል ባለመኖሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ቅስም የሰበረ ፍፃሜ ተፈፅሞ እንዳለፈ የሚታወስ ነው።  
   ዛሬ ደግሞ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ተግባር የተፈፀመበት አካባቢና ክልል ሆኖ እያለ፣ አሁንም ድንበር ጥሰው በወገኖቻችን ላይ ጥቃት በማድረስ የ18 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፉና በርከት ያሉ ህፃናትን ደግሞ አግተው ሲወስዱ አስቀድሞ የሚከላከልላቸው ታጣቂ አልተገኘም።
   ከዚህ በመነሳት ነው ለወግኖቹ ሲጨፈልቅና ሲያስር ሲያንገላታ ብቻ እንጂ የአገሩን ድንበር ጥሶ በዜጎቻችን ህይወት ላይና፣ በንብረትና በከብቶች ላይ ውድመት ለሚያደርስ ባዕድ ለወያኔ ኢህአዴግ ምንም አይደለም እያልነ ያለነው።
   ወገኖቹ በባዕድ ሃይሎች እየተጠቁ ሊያድን ያልቻለ ሰራዊት ወይም ደግሞ መንግስት ከጠላት የሚለይ ምክንያት የለውም። ይህ እንዳለ ሆኖ በመጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቆሼ በሚባል አካባቢ የተፈጠረውን የቆሻሻ መንሸራተት አደጋ ተከትሎ፣ በዜጎች ህይወት ላይ ያደረሰው ቅጥፈትና ጉዳት የሚያሳዝን ነው። በዚህ አጋጣሚ የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅን፣ ለአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን እንመኛለን። የዚህ አደጋ ዋና ተጠያቂ ደግሞ ራሱ ገዥው ስርዓት ነው።
   ምክንያቱም ከ50 ዓመታት በላይ ያህል እየተደፋና እየተከመረ የመጣና ያለ የቆሻሻ ክምር በምን ደረጃ ላይ አለ? በአካባቢው የሚኖሩ ወገኖች በምን አይነት ሁኔታ አሉ ብሎ ተገቢ ክትትልና ጥናት ተደርጎ ቦታ ቀይረው መስፈር እየተገባቸው፣ መንግስት ይህንን ባለማድረጉ የተፈጠረ አደጋ እንጂ በአንድ ቀን የወረደ ክስተት አይደለም።
   ስለዚህ በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችል የሆነ ይሁን ጉዳት ቅድሚያ ዝግጅትና ጥናት ተደርጎለት ዋስትና ያለው ቦታ ሊያገኙ ይገባል እንላለን።

No comments:

Post a Comment