በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ባለስልጣናት የሃገር ውስጥ ደህንነት ምክትል ሃላፊና የቤተመንግስት ጸጥታ ሃላፊ
የሆኑት አቶ ጌታቸው ተፈሪ ከብአዴን ጨምሮ ከሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በታማኝነታቸው ተመርጠው የሃገር ውስጥ ደህንነትን
በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ተመድበው ለ 22 ዓመታት በበላይነት ሲመሩ የቆዩ ናቸው። የቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞትን
ተከትሎ በሃገር ውስጥ ደህንነት በተደረገው አዲስ አወቃቀርና ምደባ ግለሰቦቹ ተግባብተው መስራት ስላልቻሉ በቁጥጥር ስር ውለው መጣራት
እየተደረገባቸው መሆኑን ታውቋል።
እነዚህ በሃገር ውስጥ ደህንነት ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ ግለሰቦች እንዲታሰሩ በተፈለገበት ጊዜ የኢህአዴግ ም/ቤት
በስብሰባ ላይ ነበረ። የታሰሩት የደህንነት ባላሰልጣናት ጉዳይ በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር ኅ/ማሪያም ደሳለይ ለም/ቤቱ የቀረበ
ሲሆን ገሚሱ ድጋፉን ሲሰጥ ገሚሱ ደግሞ ስለተቃወመው በመሃከላቸው ልዩነት ተፈጥሮ ሊስማሙ ስላልቻሉ በቀጥታ ወደ ድምጽ ገብተው ግለሰቦቹ
እንዲታሰሩ መደረጉን የደረሰን ዘገባ ያስረዳል።