ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን አንስተን ስንናገር በቀዳሚነት መታየት ያለበት
ነገር ቢኖር ማንኛውም በምርጫው መድረክ የሚወዳደሩ ተቃዋሚ ድርጅቶችና የግል ተወዳዳሪዎች ነፃ፤ ፍትሃዊ፤ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ
በሆነ መንገድ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውና ነፃና ፍትሃዊ ለመሆን የሚፈለገውን ምርጫ አለም-አቀፋዊ መስፈርቱን በአጠቃለለ
ሁኔታ አዋጆችን በማውጣትና ምርጫው የሚያስፈፅመው አካል ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ በማቆም ነፃ በሆነ መንገድ ምርጫን ማካሄድ
ማለት ነው።
በዚህ መለኪያ ባገራችን እየተካሄዱ የቆዩት ምርጫዎች ምን አይነት መንገድ
እየተጠቀሙ ነበር፤ የምርጫ ቦርድ አመሰራረትስ እንዴት ነበር ብለን ለማየት ብንሞክር እጅግ በርካታ ችግሮችን ማንሳት እንችላለን፣
መሰረታዊ ከሆኑትና ባገራችን የምርጫ ሂደት ትልቁ ድርሻ የሚኖረውና በቀዳሚነት የሚቀመጠው ያገራችን የምርጫ ቦርድ ህገ መንግስቱ
ላይ በተቀመጠው አንቀፅ 102 ላይ “ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት
እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል”፤በሚል መሰረት ገለልተኛና ፍትሃዊ ምርጫ
ለማካሄድ ታስቦ የቆመ ድርጅት ነው ተብሎ ቢነገርለትም በሁሉም በተካሄዱ ምርጫዎች ግን ስልጣን ላይ የሚገኘውን ገዢ ስርአት ደጋፊና
አጋፋሪ ሆኖ እየሰራ መቆይቱና አሁንም በዚሁ እየቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።
ያገራችን ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ሃላፊነትና ህዝባዊ አደራ ወደ ጎን
በመተው። የዜጎቻችን ተሳትፎ እንንዳይጨምር፤ በነጠረ ግንዛቤ የተመሰረተ የምርጫ ሂደት እንዳይከተል፤ ህብረተሰቡ መብቱና ግዴታውን
እውቆ በምርጫው ወቅት ውጤታማ ተሳትፎ እንዳይኖረው፤ምርጫውን አስመልክቶ የሚካሄደውን የትምህርትና ቅስቀሳ መድረኮች እንዳይተገበሩ
እንቅፋቶች እያካሄደ ቆይቷል፣ የዚህ ዋነኛው ምክንያትም ቦርዱ ህገ-መንግስት በደነገገው መሰረት የሚጓዝ ሳይሆን በአንድ ድርጅት
ትእዛዝ የሚሽከረከርና ነፃነት የሌለው ድርጅት ስለሆነ ብቻ ነው።
በአሁኑ ዓመት ማለትም 2007 ዓ/ም በሚካሄደው አስመሳይ ምርጫ ላይ
ካለፉት ጊዜያት በተለየ መንገድ ይሰራበታል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም፣ በየአመቱ በመገናኛ ብዙኃንና በተለያዩ መድረኾች ተቀዋሚ ድርጅቶችን
ለማጠናከር መንግስት ልዩ ድጋፍ ያደርግላቸዋል ተብሎ ቢነገርም ገና ምርጫው ሳይካሄድ ጀምሮ ከመጠን በላይ አፈናዎች እየተፈፀሙ በመሆናቸው
እየተሰጠ ካለው ባዶ ቃል የሚስማማ ሆኖ አልተገኘም።
ባለፉት
ቅርብ ቀናት በአዲስ አበባና ሌሎች ክልሎች በተቃዋሚ ድርጅቶች አባላትና አመራሮች ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን የማዋከብ ሁኔታና በምርጫው
ዋዜማ የሚካሄዱትን ሰላማዊ ሰልፎችና አላማቸውን ለህዝቡ የማስተዋወቅ እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ሰይጣናዊ ምክንያቶችን በመደርደር እያሰናከሏቸው
ያሉበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ገዢው የወያኔ ኢህአዴግ መንግስት ምርጫውን በማስመልከት ከለይ እስከ ታች
የሚገኙ የመንግስት አመራሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል ለመቀስቀስ ተከታታይ ስብሰባዎች እያካሄደ ባለበት ባሁኑ ሰዓት ተቃዋሚዎች
ድርጅቶች ተመሳሳይ ስራ ለማካሄድ ፍቃድ በሚጠይቁበት ሰአት እንዲከለከሉ፤ ወከባ እንዲደርስባቸውና እንዲታሰሩ ማድረግ መንግስት ለተቃዋሚዎች
ልዩ ድጋፍ እያደርኩላቸው ነኝ የሚለውን የሚያመለክት ሳይሆን የተለመደው አስመሳይ ንግግሩን ይበልጥ የሚያጋልጥና በሚያራምደው አፋኝ
አካሄድ የሚረጋገጥ ዴሞክራሲያዊና ፍትሓዊ ታማኝ ምርጫ እንደማይኖር የሚያሳይ ነው።