Tuesday, December 23, 2014

በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል በሚኖሩ አርሶ አደሮች እያጋጨ የቆየውን መሬት ችግሩን ለመፍታት በሚል ምክንያት ከሁለቱም ክልሎች የተወጣጡ ባለስልጣናት ወደ ቦታው በሄዱበት ሰዓት በአካባቢው ማህበርሰብ ተቀባይነት ማግኘት እንዳልቻሉ ለማወቅ ተችሏል።



    ምንጮቻችን ከአካባቢው የላኩልን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል በሚኖሩ ገበሬዎች ላይ ግጭቶችን እየፈጠረ የነበረውን መሬት ለመፍታት በሚል ከትግራይ ክልል ኪሮስ ቢተው   የትግራይ ክልል የግብርና ቢሮ ሓላፊ፤ ዘአማኔኤል ለገሰ (ወዲ ሻንበል) የፖሊስ ኮሚሽን ሓላፊ፤ ሓዲሽ ዘነበ የፀጥታ ሓላፊ ሲሆኑ፤ ከአማራ ክልል ደግሞ የግብርና ቢሮ ሓላፊውና ይሳቅ አያሌው የፀጥታ ሓላፊው፤ የፖሊስ ኮሚሽን ተወካይ መሓመድ ከድር ከታህሳስ 4 እስከ 5 2007 ዓ,ም ችግሩ ወደ ተከሰተበት ቦታ ሄደው የሰነበቱ ቢሆኑም ያለምንም መፍትሄ እንደተበተኑ ለማወቅ ተችሏል።
 ባለስልጣኖቹ የሄዱበት ቦታ ደግሞ ግጨውና አከባቢው ማርዘነብና  አካባቢ እንዲሁን ማይእንጓና አከባቢው ሲሆን ከአሁን በፊት እናርሳለን አታርሱም በሚል በሁለቱ ክልል ገበሬዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የፌደራል ፖሊስ ጭምር መሞታቸውን የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይ በአማራ ክልል የሚገኙ ገበሬዎች መሬቱ በክልላችን ስለሚገኝ እናርሰዋለን በማለታቸው ምክንያት የመሬት ማካለሉ ውሳኔ መቅረቱን ለማወቅ ተችሏል።
  መረጃው አክሎ እንዳስረዳው እንደመፍትሄ ተብሎ በስርዓቱ ካድሬዎች በቀረበው ሃሳብ ያልተደሰተው ማህበረሰብ እናንተ መሬቱን አካልላችሁ ልታስታርቁን ሳይሆን እራስ በራሳችን ልታገዳድሉን ነው የመጣችሁ እየተገዳደልነም ብንሆን እንኖራለን እንጂ ውሳኔአችሁን አንቀበለውም ካሉ በኋላ  ኪሮስ ቢተውና ያማራ ክልል የግብርና ቢሮ ሃላፊም ውሳኔአችንን ካልተቀበላችሁት ይህ መሬት ካሁን በኋላ ከሁለቱም ክልል ውጭ ሁኖ በፌደራል እንዲተዳደር ተወስኗል በማለታቸው ህብረተሰቡ በበኩሉ ያስተላለፉትን ውሳኔ እንዳልተቀበለው ምንጮቻችን አክለው አስታውቀዋል።