በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ የሚገኙ አጠቃላይ የከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤት ሰራተኞችን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ
ዘለቀ አንሉ ሰብስቦ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ.ን ምረጡ የሚል ቅስቀሳ ያካሄደ ሲሆን ከተሰብሳቢው የተሰጠው ምላሽ ግን በእጅጉ በርካታ የስርዓቱ
ካድሬዎችንና አመራሮችን እንዳስቆጣ ለማወቅ ተችሏል።
ቀበሌ 01 በሚገኘው ጃቢ ጠህናን አዳራሽ የተካሄደው ቅስቀሳ የከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤት የመንግስት ሰራተኞች በሙሉ
በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲወጡ በሚል ትዕዛዝ የተገኙ ሲሆን የዋና አስተዳዳሪውን የምረጡን ጥሪም በርካታዎቹ የተቃወሙት ሲሆን በተቃውሞነት
ከተሰነዘሩ ሃሳቦች መካከልም የስኳርና የዘይት ሽያጭን በተመለከተ ለምን ለድርጅት ደጋፊዎች ብቻ ይሸጣል? በከተማችን ያለ አግባብ
የሚታሰሩት ዜጎች የመልካም አስተዳደር ማሳያ ናቸው ወይ? ከተማችን እንደዞን ከተማ በርካታ የመሰረተ ልማት አውታሮች ይጎድሏታል?
ስለዚህ ለውጥ እንፈልጋለን የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች መነሳታቸውን ምንጮቻችን ጨምረው አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከሚያዝያ 26 ቀን 2007
ዓ/ም ጀምሮ በዞኑ ከተሞች የመብራት መቆራረጥ ችግር የተከሰተ ሲሆን
የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ ሊያስቀምጡ ባለመቻላቸው በኤሌክትሪክ ሓይል የሚሰሩ ድርጅቶች ለኪሳራ እየተጋለጡ መሆናቸውን ለማወቅ
ተችሏል።