ያገራችን የትምህርት ፖሊሲ ለ24 አመታት ያህል ትውልድ ገዳይ ሆኖ እየቀጠለ
መሆኑን ሁሉም ዜጋ ስለሚያውቀው ሁኔታውን አስመልክቶ ለማስረዳት መሞከሩ ለቀባሪ ማርዳት ነው የሚሆነው።
ትምህርት ያገራችንን ሰዎች በመገንባትና ማህበራዊ ሁኔታቸውን በማሻሻል፤
እቅድ በማስያዝና ባገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ህይወት ውስጥም ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄና ብቃት መታቀድ ያለበትና በአተገባበሩም
በደመ ነፍስ አደጉ ከሚባሉ ሃገሮች እየተኮረጀ ተግባር ላይ በማዋል ሳይሆን ብቃት ያላቸው ያገሪቱ ምሁራን የሚሳተፉበት ፖሊሲ በመቅረፅ
ለውጤት መንቀሳቀስ የሚጠይቅ ነው።
ባሁኑ ግዜ ባገራችን ውስጥ እየተሰራበት ያለው የትምህርት ፖሊሲ በተለይ
የኢህአዴግ ስርዓት በትምህርት ዝግጅት ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋትና አደጋ ከተጠያቂነት ነፃ ሊያደርገው አይችልም ብቻ ሳይሆን ስርዓቱ
ለ24 ዓመታት ያህል በተከተለው የተበላሸ የትምህርት ፖሊሲ ምክንያት ኢህአዴግ ላይ ተስፋ የቆረጠበት ሁኔታ ነው ያለው።
የኢህአዴግ ስርዓት ገና ስልጣን እንደተቆጣጠረ የትምህርት ፖሊሲ ማዘጋጀት
በጀመረበት ግዜ የፈጸመው ደባ ማለትም ፖሊሲውን የማርቀቅ ሃላፊነት ከትምህርት ሚኒስተር ቢሮና ከምሁራኑ እጅ አስወጥቶ በጠቅላይ
ሚኒስተር ቢሮ እንዲመራና ከትምህርት ጋር ግንኝነት የሌላቸውን ቢሮክራቶችና የስርዓቱ ካድሬዎች እንዲያዘጋጁት የተደረገበት ሁኔታ
እንደነበረና እስካሁንም ምንም አይነት ማሻሻል ሳይደረግበት እየቀጠለ በመሆኑ ባገራችን ውስጥ ያለው የትምህርት ሁኔታ በፖለቲካ ቅኝት
የሚመራና ብቃት ያላቸው የተማሩ ወገኖቻችንን በማፈናቀል ካድሬዎቹ ቦታውን እንዲቆጣጠሩት ከማድረጉ በላይ ስርአቱ አንድ ለዓምስት
የሚለውን አደረጃጀት በመፍጠር። በተማሪው መካከል ኮራጅና አስኮራጅ እንደ ሰደድ እሳት እንዲስፋፋና በቂ እውቀት ያለው ተማሪ ማፍራት
እንዳይቻል ምክንያት ሁኗል።
የመምህራን ነፃነት በተመለከተም ባለቤት ያጣ፤ መምህሩ በነፃነት ለመደራጀትና
ከዚህ በፊት የነበረውን ማህበር በማፈራረስ ስርአቱ የሱ አምሳያ በሆኑት ካድሬዎች የሚጠመዘዝ ማህበር እንዲቋቋም በማድረጉ ምክንያት
በተለይ አስተማሪው መብቱን በሚያስከብርበት መንገድ እንዲደራጅ እድል እንዳላገኘና ከስርአቱ ጋር ጥልቅ ግንኝነት ባላቸው ካድሬዎች
እየተመራ ወደደም ጠላም የስርአቱ አገልጋይ እንዲሆን በሚያስገድድ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይ መልኩ የተማሪዎች ነፃ ማህበርና እንቅስቃሴ የሚባልም የለም
በዩኒቨርስቲዎችና በሌሎች ከፍተኛ ት/ቤቶች የድሮ ተማሪ ያለፈበትን በተነፃጻሪ ነጻ ሁኖ የመንቀሳቀስ እድል እንዳያገኝ፤ የመሰለውን
እንዳይጠይቅና መብቱን ለማስከበር እንዳይደራጅ፤ ፖለቲካዊ አስተሳሰቡ እንዳይሰፋና የስርአቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ አውቆ ለለውጥ
እንዳይነሳ ሆን ተብሎ የትምህርት ዘርፎቹ እንዲዳከሙ በማድረግ ተመሪዎቹ እንዲደነዝዙ ተደርጓል።
ለማጠቃለል።-
- ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ አስተማሪውን ለመጉዳት ሆን ተብሎ ያለ
በቂ ደመወዝ እንዲሰራ በተደረገበት ግዜ ማለት ከ20 ዓመት በላይ ያስተማረ አስተማሪ ከአንድ የቀበሌ ካድሬ እንኳን ሲወዳደር አንድ
ሦስተኛ ያህል ደመወዝ በማይከፈልበት ወቅት፤
- ስርዓቱ ለአስተማሪው ከፍተኛ ደመወዝ እንደጨመረ
አድርጎ ይናገር እንጂ። ተደረጓል የተባለው ጭማሪ ግን 73 ብር ብቻ በመሆኑ፤ በመምህሩ ላይ የነበረው ንቀት በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠሉና
የተፈጸመውን አሳዛኝ ድርጊት የተቃወሙት መምህራንም የተለያየ ስም ከጀርባቸው እየተለጠፈ ልክ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ውስጥ እንደሚደረገው
ከስራቸው እንዲባረሩ እየተደረገ ባለበት ባሁኑ ግዜ ባገራችን ጤነኛ የትምህርት ስርዓትና ፖሊሲ መፍጠር አይቻልም ብቻ ሳይሆን የዜጎቹን
የመማር ፍላጎት ጭራሹን የሚገድል አካሄድ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።