በደረሰን ዘገባ መሰረት የጉምሩክና ገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትርንና ምክትላቸውን ጨምሮ በርካታ የበታች ሹማምንቶች
፤ የመንግስት ሰራተኞችና ትላልቅ ነጋዴዎች ካለፈው ወር ጀምሮ በሙስና ተከሰው በእስር ላይ መሆናቸውን የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ
የስርዓቱ ባለስልጣናት ሰዎቹ የታሰሩት በሙስና ሳይሆን በፖለቲካ ምክንያት ነው የሚል አመለካከት በመያዛቸው በኢህአዴግ ውስት ከፍተኛ
ውጥረት ተፈጥሯል።
በተፈጠረው የሃሳብ ልዩነት ምክንያት በባለስልጣናቱ መካከል አለመተማመን ተፈጥሯል ። እስካሁን ድረስም መግባባት
እንዳልቻሉ ዘገባው ጠቅሶ ፤ በአሁኑ ጊዜ በሙስና ሽፋን እየተወሰደ ያለው የእስራት እርምጃ በመቃወም ላይ ያሉ ባለስልጣናት መንግስት
ሙስናን ለመዋጋት ፍላጎት ኖሮት ሳይሆን በሙስና ስም ሰዎችን ለማጥቃትና ከህብረተሰቡ ለመነጠል በተጨማሪም በዚሁ መንገድ መንግስት
ሙስናን በመዋጋት ላይ እንዳለ መስሎ ለመታየት የሚያደርገው ጥረት ነው የሚል አቋም በመያዛቸው ምክንያት ልዩነታቸውን ማጥበብ እንዳልቻሉ
ለማወቅ ተችሏል ።
ይህ በእንዲህ እያለ ከታሰሩት 58 ባለስልጣናት ሌላ የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ ካሉ ድርጅቶች ጋር ግንኝነት
አላቸው የተባሉ 20 ሰዎች በመጥፎ አያያዝ ተይዘው ልዩ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ቷውቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት በባህርዳር ከተማ የተቃጠለውን የእጣንና ሙጫ ፋብሪካን አሸባሪዎች አቃጠሉት
ሲል ኢህአዴግ ቢገልጽም ሃቁ ግን በኢህአዴግ አመራሮች መካከል በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት እራሱ ኢህአዴግ ያሰማራቸው ሰዎች አቃጥለውታል
የሚል መረጃ መኖሩን የደረሰን ዘገባ ጨምሮ ያስረዳል።